በዓለም በርካታ መፈንቅለ መንግሥታትን ያስተናገደችው አገር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የላቲን አሜሪካዋ ቦሊቪያ ከአውሮፓውያኑ 1950 ጀምሮ በዓለም ላይ ከፍተኛ መፈንቅለ መንግሥታት ያስተናገደች አገር ሆናለች።
በቅርቡ ወታደሮች የአገሪቱ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ዋና ከተማዋ ላፓዝ የሚገኘውን የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ለሰዓታት ተቆጣጥረው ነበር።
የቦሊቪያ ፖሊስ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው መሪ የሆኑትን የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሁዋን ጆሴ ዙኒጋን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ አስታውቋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮች እና ተሽከርካሪዎች በርካታ ቁልፍ መንግሥታዊ ህንጻዎች የሚገኙበትን ሙሪሎ አደባባይን ከበው ታይተዋል።
አንድ የታጠቀ ተሽከርካሪ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት መግቢያ በር ጥሶ ለመግባት ሲሞክር ታይቷል። በኋላም ወታደሮች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል።
በአገሪቷ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መነሻ የሆኑ ሦስት ምክንያቶችን እንጥቀስ።
የመፈንቅለ መንግሥታት ታሪክ
በቅርቡ ሥልጣንን በኃይል ለመጨበጥ የተደረገው ሙከራ አገሪቷ ያሳለፈችውን የጨለማ ዘመናትን ተውስታ ቀስቅሰዋል።
ወታደሮች በሕዝብ የተመረጡ መንግሥታትን ከሥልጣን የሚገረስሱበት እና አገሪቷ ከአውሮፓውያኑ 1950 ጀምሮ ለሰባት አስርት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችበት ታሪክ አላት።
በአሜሪካ ጉዳዮች የመረጃ ተንታኞች የሆኑት ጆናታን ፓውል እና ክሌይተን ቲይን እንደሚሉት በቦሊቪያ ባለፉት 74 ዓመታት ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክረው ግማሾቹ ከሽፈዋል።
ፓውል ለቢቢሲ ሙንዶ እንደተናገሩት ቦሊቪያ በዓለም ላይ በርካታ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባት አገር ሳትሆን እንደማትቀር ነው።
ነገር ግን ከአውሮፓውያኑ 1950 በፊት ያሉ አስተማማኝ መረጃዎችን ማግኘት ከባድ ነው።
ተንታኞች እንደሚናገሩት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን መቁጠር ከበድ የሚያደርገው በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት፣ ማኅበራዊ አመጽ እና ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣንን መቆጣጠር በሚሉት እሳቤዎች መካከል ያለው ልዩነት መጥበብ ነው።
በላቲን አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 1900 ጀምሮ ወደ 320 የሚጠጉ ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እንደተካሄዱ በሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ፋብሪስ ሌሆውክ ያስረዳሉ።
ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ እንደተሳኩ የሚያስረዱት ፋብሪስ ቦሊቪያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ካደረገችው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ፕሬዚዳንቶቹን ከሥልጣን ለማውረድ ችለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርብ ጊዜው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መነሻ ምንድን ነው?
በቅርቡ ከኃላፊነታቸው እስኪነሱ ድረስ የአገሪቱን ሠራዊት ይመሩ የነበሩት ጄኔራል ሁዋን ጆሴ ዙኒጋ ባለፈው ሳምንት የተሞከረው የመንግሥት ግልበጣ መሪ ናቸው።
ጄኔራሉ የቀድሞ የቦሊቪያ ፕሬዚዳንት ኢቮ ሞራሌስ አገሪቱ በአውሮፓውያኑ 2025 በምታደርገው ምርጫ የሚወዳደሩ ከሆነ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውሏቸው አስፈራሩ።
ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ አገሪቷን ለሦስት ጊዜ የመሩት ኢቮ ሞራሌስ ለአራተኛ ጊዜ እንዳይወዳደሩ ፍርድ ቤት እግድ ጥሎባቸዋል።
ጄኔራሉ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ማስፈራራታቸውን ተከትሎም ነው የአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት ሉዊስ አርቼ ከኃላፊነታቸው ያሰናበቷቸው።
ጄኔራሉ ይህንን ያሉት የአገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስከበር ነው ብለዋል።
በኋላም ጄኔራሉ በፕሬዚዳንቱ ጥያቄ ጦሩ ጣልቃ መግባቱን ለሚዲያ ከተናገሩ ከደቂቃዎች በኋላ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት መርተዋል በሚል በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፕሬዚዳንት ሉዊስ አርቼ ድርጊቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው በማለት አውግዘው፤ ሕዝቡ እንዲደራጅ እና ለዲሞክራሲ እንዲወግን ጥሪ አቅርበዋል። የጦሩ አዛዝ ዙኒጋ የአርቼ አስተዳደር ሕዝቡን “እያደኸየ” እንደሆነ በመጥቀስ ጣልቃ መግባታቸው ተጠቅሷል።
ጄኔራሉ አገሪቷ እየገጠማት ካሉ የምጣኔ ሀብቶች ተግዳሮቶች በተጨማሪ ሠራዊቱ “ዲሞክራሲን ለመመለስ እና የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት እየሞከረ ነው” ሲሉ ተናግረው፤ መፈንቅለ መንግሥቱ ዲሞክራሲን እውን በማድረግ አገሪቱ ለአስርት ዓመታት በተመሳሳይ ሰዎች የምትመራበትን ሂደት ያከትማል ብለዋል።
አገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮ ግራ ዘመም በሆነው ሙቭመንት ፎር ሶሻሊዝም (ማስ) ፓርቲ ስትመራ ቆይታለች።
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦሊቪያውያን መንግሥትን ለመደገፍ ወደ አደባባዮች ወጥተዋል። ይህ አለመረጋጋት የተከሰተው የአገሪቱ ውጥረት እየተባባሰ ባለበት ወቅት ነው።
የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና በአሁኑ መሪ አርቼ እና በቀድሞው ፕሬዚዳንት መካከል ያለው የከረረ የፖለቲካ ፉክክር ባለፉት ወራት ውስጥ በፓርቲው መካከል መከፋፈል እና በርካታ ሰልፎች እንዲታዩ ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአርቼ እና የሞራሌዝ ፉክክር
የቀድሞ የፖለቲካ አጋር የነበሩት ፕሬዚዳንት አርቼ እና የቀድሞው መሪ ሞራሌስ በሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ያሉ ይመስላል።
ሁለቱም ሞቪሚየንቶ አል ሶሺያሊዝሞ (ሙቭመንት ፎር ሶሻሊዝም) የተሰኘው የግራ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኝ ፓርቲ አባላት ናቸው።
በሁለቱ ፖለቲከኞች መካከል ሽኩቻ የተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ቢከለክላቸውም ሞራሌስ በቀጣዩ ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ማወጃቸውን ተከትሎ ነው።
ፍርድ ቤቱ የሥልጣንን ዘመንን መገደብ አንዳንዶች ለረዥም ዘመናት በሥልጣን ላይ እንዳይቆዩ ለማረጋገጥ እንደሆነም ጠቅሷል።
ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆዩት ሞራሌስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማጭበርበር ሞክረዋል በሚል ውንጀላ በወታደራዊ አዛዦች በአውሮፓውያኑ 2019 ከሥልጣን እንዲወርዱ ተደርገዋል።
ይህንን የሚያስተባብሉት ሞራሌስ ግን ከኃላፊነታቸው ተነስተው ከአገር ወጡ።
የሳቸውን መውረድ ተከትሎም ለአንድ ዓመት ያህል ጂያኒን አኔዝ የአገሪቱ ጊዜያዊ መሪ ሆነች።
በኋላ ግን ሞራሌስን ከሥልጣን ለማውረድ መፈንቅለ መንግሥት አድርጋለች በሚል ክስ የ10 ዓመት እስር ተፈረደባት። ድጋሚ ምርጫ ተደርጎ የአሁኑ የአገሪቱ መሪ አርቼ አሸንፈው ፕሬዚዳንት ሆኑ።
ሞራሌስ አገሪቱ በቀጣዩ ምርጫ በምታደርገው ምርጫ መሳተፍ ካልቻሉ “ሕዝባዊ አመጽ” እንደሚያስነሱ እና ፕሬዚዳንት አርቼንም ዕጩነታቸውን ለማስቆም እየሞከሩ ነው በሚል ከሰዋል።
ከአገሬው ቀደምት ማኅበረሰብ የወጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት ሞራሌስ በአሁን ወቅት ተወዳጅነት ያላቸው እና አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ናቸው።
ሞራሌስ ፕሬዚዳንቱ እና ጄኔራሉ የሚሳተፉበት ሴራ እየተጠነሰሰባቸው እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ተሞከረ የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ሞራሌዝ የቦሊቪያ ሕዝብ ዲሞክራሲን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም ወታደሩ ሥልጣን እንዳይቆጣጠር እና እስከ መጪው ምርጫ የአርቼ አስተዳደር በመምራት እንዲቆይ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት አርቼ የአገሪቱን ጦር እንዲመሩ ጄኔራል ሁዋን ጆሴ ዙኒጋን የሾሙት በአውሮፓውያኑ 2022 ነበር። ጄኔራሉም ሆነ ፕሬዚዳንቱ ሞራሌዝን በመተቸት ይታወቃሉ።
ጄኔራሉ የቀድሞው ፕሬዚዳንት “ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት እንዳይገረስሱ” እንደሚከላከሉ በቴሌቪዥን በተደረገ ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን በቁጥጥር ስር ሲውሉ ፕሬዚዳንት አርቼ ተወዳጅነታቸውን ለመጨመር መፈንቅለ መንግሥቱን አቀነባብረዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል። ይህንን ውንጀላቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ግን ማቅረብ አልቻሉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቦሊቪያ “የምጣኔ ሀብት ተዓምር” ስጋት
ይህ ሁከት የተነሳው ቦሊቪያ ውስብስ በሆነ የምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ ዳራ ውስጥ ባለችበት ነው።
ለዓመታት ያህልም ምጣኔ ሀብቷ በላቲን አሜሪካ ካሉ አገራት መካከል የጎላ ነበር።
ስር በሰደደ የዋጋ ግሽበት ከሚሰቃዩት ጎረቤቶቿ በተለየ በፈጣን እድገት፣ መረጋጋት እና ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት በማስመዝገብ ላይ ነበረች።
ነገር ግን ቦሊቪያ በላቲን አሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ድህነት ከሚታይባቸው አገራት አንዷ ናት።
የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው 'ዘ ቦሊቪያን' በማሽቆልቆሉ ምክንያት በርካታ ሰዎች የሚገበያዩት በአሜሪካ ዶላር ነው።
ነገር ግን የአሜሪካ ዶላር እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች “የቦሊቪያ የኢኮኖሚ ተዓምር” ብለው የሚጠሩት እድገት ስጋት ተደቅኖበታል።
የአሜሪካ ዶላር እጥረት በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን፣ ቦሊቪያውያን እንደ ሩዝ እና ቲማቲም ያሉ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ለመግዛት አዳጋች አድርጎባቸዋል።
የአሜሪካ የዶላር እጥረት በከፊል በአገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት መውደቅ ምክንያት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የቦሊቪያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጄይሚ ደን ያስረዳሉ።
የቀድሞው መሪ ሞራሌስ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ጋዝ ኢንዱስትሪን ብሔራዊ እንዲሆን ያደረጉት በአውሮፓውያኑ 2006 ነው።
ሞራሌስም ይሁኑ ፕሬዚዳንት አርቼ የመንግሥት ድጎማ ያለበትን የነዳጅ ግዢ መርሃ ግብርንም ሆነ ትልልቅ የሕዝብ ማኅበራዊ ዕቅዶችን ለመደገፍ የአሜሪካ ዶላር ይጠቀማሉ።
“ይህ በአገሪቱ ውስጥ ቀውስ አስከትሏል። ምንም እንኳን የመንግሥት ገቢ ቢቀንስም ወጪው በጣም ከፍተኛ ሆኖ ቀጥሏል። ከ[አውሮፓውያኑ] 2014 ጀምሮ የተፈጥሮ ጋዝ ገቢ በውጭ እና በውስጥ ዕዳ ተተካ” ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጄይሚ ያስረዳሉ።
ቦሊቪያ 56 በመቶ ቤንዚን እና 86 በመቶ ናፍጣ ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባ ፕሬዚዳንት አርቼ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የሚያስፈልጋትን የነዳጅ ምርት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በቂ ዶላር እንደሌላት ባለሙያዎች እያስጠነቁ ሲሆን፣ ይህም ለበርካታ ሕዝባዊ ሰልፎች መነሻ ሆኗል። የተለያዩ አገራት መሪዎች በቅርቡ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዘዋል።
ተንታኞች በቅርቡ የተከሰተው ያልታቀደ፣ ለአጭር ጊዜ የቆየ እና ብዙም ግምገማ ያልተደረገበት ወታደራዊ አመጽ እንጂ ሰፋ ያለ የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን የሚያሳይ ነገር የለም ባይ ናቸው።












