ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ችግሯን በራሷ ሥርዓትና ቀኖና እንድትፈታ እንዲደግፏት ለአገሪቷ መሪዎች ጥሪ ቀረበ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሞኑ የተፈጠረውን ችግር በራሷ ህጎችና ቀኖና እንድትፈታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለኢትዮጵያ አመራሮች ጥሪ ቀረበ።
ጥሪውን ያቀረበው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ለቤተ ክርስቲያኗ አጋርነቱን በገለጸበት በሰሞኑ መግለጫው ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህጋዊ እውቅና ያላት የሃይማኖት ተቋም መሆኗን ያተተው ምክር ቤቱ “ቤተ ክርስቲያኗ በምዕመናኖቿ መካከል አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ ለመቅረፍ ያስችላት ዘንድ በኢትዮጵያ የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮች ድጋፋችሁን ስጧት” ሲሉም የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ ቄስ ጄሪ ፒላይ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽእኖ የሚያደርስና አንድነቷንም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸውም ዋና ጸሃፊው በምክር ቤቱ ድረ ገፅ ላይ በወጣው መግለጫቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን "ጥንታዊና ለአንድነትና ለሰላም የደም ዋጋ ጭምር በመክፈል ስትሰራ ነው የኖረው ሲሉ የጠቀሱት” ቀሲሱ “ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከፍሎ አዲስ ሲኖዶስ የመቋቋም ሁኔታውም ምክር ቤቱን አሳዝኗል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቷ ህግ፣ ቀኖና ስርዓት ላይ ብቻ በተመሰረተ መልኩ እንዲፈታ መስራት እንደሚገባ ለፌደራልና ለክልሎች መንግሥታት ጥሪ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ ጥሪ አቅርቧል።
ጉባኤው ህገ መንግሥቱንም በመጥቀስ መንግሥታቱ ይህንን ማዕከል ባደረገ መልኩ ተከትለው እንዲሰሩ ነው ለተለያዩ አመራሮች ያሳሰበው።
ቤተ ክርስቲያኗ ዘመናትን የተሻገረ ቀኖናና ስርዓት ያላት አንጋፋ ተቋም ከመሆኗ አንጻር አሁን ያጋጠመው ውስጣዊ ችግር በቤተክርስቲያኒቱ ህግና ስርዓት ሊፈታ እንደሚችልም ይጠብቃል ብሏል።
ጉባኤው ባወጣው መግለጫው ለቤተ ክርስቲያኗ አባቶችም መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን “ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ከማስከበር ጎን ለጎን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ተገንዝባችው ውይይትን ይቅርታን እርምትን እንድታስቀድሙ” ሲልም ተማጽኗል።
በተጨማሪም ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችም ቤተ ክርስቲያኗ የተፈጠረውን ችግር በራሷ ልትፈታ እንደሚገባ አምነው ይህንን ችግር ከማባባስ እንዲቆጠቡም ጠይቋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር፣ የመከፋፈል አዝማሚያና ይህንንም ተከትሎ እየተከሰቱ ያሉ ጉዳዮች አሳዛኝ መሆኑንም የገለጸው ጉባኤው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችም ጋር ችግሩ በሰላማዊ ሁኔታ ስለሚፈታበት ሁኔታም መወያየታቸውንም ጉባኤው አትቷል።
ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ውጪ የተሰጠውን የጵጵስና ሹመት ተከትሎ የተፈጠሩ አለመግባባቶች እየተባባሱና እየተካረሩ ሄደዋል።
ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ስርዓትና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።
የቤተ ክርሰቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።