ቤተክርስቲያን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን እና ሥርዓቷን ያከበሩ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት ፡ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከተከታዮቿ የሚቀርቡ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን እና ሥርዓቷን እንዲሁም አንድነቷን ያከበሩ ጥያቄዎችን ለማስናገድ ዝግጁ መሆኗን የቤተከርስቲያኗ መሪ ተናገሩ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሰኞ የሚጀመረውን የአብይ ጾምን አስመልከተው “ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት ላይ “ከቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓት መከበር እንደዚሁም ከሉዓላዊ አንድነቷ መጠበቅ በመለስ” ያለን ጥያቄ ለማስናገድ ቤተ ክርስቲያኗ ዝግጁ ናት ብለዋል።

ይህ የፓትሪያርኩ ንግግር ጥያቄ አለን በማለት ከሳምንታት በፊት ሦስት ጳጳሳት ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ አጋጥሞ የነበረውን ቀውስ መሠረት ያደረገ ነው።

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና እና ሥርዓት የጣሰ ነው ባለው ሁኔታ ሦስቱ አባቶች 26 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾማቸው ከቤተክርስቲያኗ ተወግዘው እንዲለዩ ወስኖ እንደነበር ይታወሳል።

ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው ላይ ጨምረውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕዝቦች በቋንቋቸው የመማር፣ የማስተማርና የማምለክ እንዲሁም የመተዳደር መብትን “ካሁን በፊትም፣ አሁንም፣ ከአሁን በኋላም የምትነፍግበት መሠረት የለም” ብለዋል።

በኦሮሚያ እና በደብብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ምእመናን በቋንቋቸው የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት እያገኙ አይደለም በዚህም በርካቶች ወደ ሌላ እምነት እየሄዱ ነው የሚልና ሌሎችም ጥያቄዎችን ያነሱ አባቶች በወሰዱት እርምጃ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።

ይህንንም በተመለከተ ፓትሪያርኩ “በቋንቋ የመጠቀም መብት በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን...ውስጥ በሚገባ ተቀምጦ ይገኛል” በማለት፤ ሁሉም በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ በሕግ ደረጃ ተመልሶ በተግባር እየተሰራበት የሚገኝ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ችግር የቤተ ክርስቲያናኗን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና ባሕላዊ መርኅን የናደ እንደነበር የጠቀሱት ፓትሪያርኩ፣ ይህም “በኢትዮጵያ ይቅርና በዓለም ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ድርጊት” መሆኑን ገልጸዋል።

ለሳምንታት በዘለቀው ውዝግብ “የቤተ ክርስቲያን ድምፅ በመስማት እና በመቀበል ሕዝበ ክርስቲያኑ እና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር ባቀረቡት ሐዘን እና ፀሎት ስህተቱ ሊታረም ችሏል” ብለዋል አቡነ ማትያስ።

የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት የማቀራረብ ጥረት ችግሩ ተፈትቶ በውግዘት ከቤተክርስቲያኗ ተለይተው የነበሩት አባቶች እንዲመለሱ ተደርጎ ውጥሩ ረግቧል።

ፓትሪያርኩ ይህንን በሚመለከትም “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና መንግሥታቸው፣ ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት እና ሉዓላዊነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለከፈሉ ምእመናን እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን ተሰልፈው ድምጻቸውን ላሰሙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ምስጋና አቅርበዋል።

አቡነ ማቲያስ ሰኞ ስለሚጀመረው ጾም ባስተላለፉት መልዕክትም ምዕመኑ የሚያደርጋቸው ነገሮች ፍቅርን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበው “መጠራጠርን እና አለመተመማንን የሚያስቀር፣ የተለያዩትን የሚያቀራርብ፣ የተሳሳቱትን የሚያርም” መሆን እንደሚገባው መክረዋል።

ጨምረውም በአገሪቱ እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭል እና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌ በእጅጉ ጠቃሚ እና ለሁለገብ የአገሪቱ ልማት እና ዕድገት እንዲሁም ለተሟላ አንድነት ጠቃሚ በመሆኑ “እግዚአብሔር ለዘለቄታው እንዲያሳካው” ምእመኑ በጾሙ ወቅት በጸሎት እንዲለምን ጥሪ አቅርበዋል።