የትግራይ አስተዳደር የማያውቀውን ስብሰባ በጠሩ ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ

በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የማያውቀው በህወሓት የተጠራ ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪ ሲያደርጉ በነበሩ የክልሉ መስተዳደር ባለሥልጣናት ላይ “እርምጃ” መወሰዱን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ አርብ ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ባለሥልጣናት መቀለ ውስጥ ስብሰባ ለማድረግ ከረቡዕ ሌሊት ጀምሮ እየተነቀሳሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“መንግስት በማያውቀው፣ የሕዝብ ሃብት በማባከን ከረቡዕ ጥቅምት 14/2016 ዓ/ም እኩለ ሌሊት ጀምሮ፤ ከጣቢያ፣ ከወረዳ እና ከዞን የተሰባሰበ ኃይል ወደ መቀሌ ለስብሰባ የተጠራበት ምክንያት ግልጽ አይደለም” ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ክልሉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለስብሰባ ወደ መቀለ በመምጣት የክልሉ መስተዳደር የማያውቀውን ስብሰባ ማካሄድ ዓላማው ግልፅ አይደለም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በማለት የመንግሥትን አሰራር በጣሱት ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

“የሰብሰባው ዋና ተሳታፊዎች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊዎች ሲሆኑ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያልተወጡት ላይ እርምጃ ተወስዷል” በማለት እርምጃው እንደሚቀጥልም አስጠንቅቀዋል።

በህወሓት ለተጠራው ስብሰባ ከአንዳንድ አካባቢዎች ለሚመጡት ሰዎች “ስንቃቸውን ጭምር ይዘው እንዲመጡ” እንደተነገራቸው አቶ ጌታቸው ጠቅሰው፣ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ኃላፊዎች “ሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለባቸው፤ ይህንን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ላይ ጠንካራ ሕግን የማስከበር እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ስብሰባው በምሽት ስለመጠራቱ፣ ተሳታፊዎቹ ከየት እንደመጡ እና ስለተወሰደው እርምጃ ከመግለጽ ውጪ የስብሰባው ዓላማው ምን እንደሆነ ማብራሪያ አልሰጡም።

ትላንት የክልሉ መገናኛ ብዙኃን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የስድት ዞኖች የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊዎችን ከኃላፊነታቸው ማንሳታቸው ዘግበዋል።

ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም. ህወሓት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በኩል ባሰራጨው መልዕክት ላይ ደግሞ፣ ቅዳሜ እና እሁድ የበመቀለ ከተማ ስብሰባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ህወሓት “የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈጻሚ እና የተለያዩ ኮሚቴዎች በወሰኑት መሠረት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ካድሬዎች ስብሰባ እንደሚያካሂዱ” በመግለጽ ሕዝቡ ስብሰባውን በሚመለክት የሚነዙት አሉባልታዎችን እንዳይሰማ አሳስቧል።

ከአንድ ዓመት በፊት ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቋቋመው በአቶ ጌታቸው የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ካሉ ተለያዩ ወገኖች ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

በዚህ ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አቶ ጌታቸው የሚመሩት አስተዳደር በዞኖች እና በወረዳዎች ውስጥ እግሩን መትከል አለመቻሉን እና አንዳንድ ወረዳዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል መሆናቸውን እንዳይቀበሉ የሚያደርግ “የተደራጀ እንቅስቃሴ” እንደነበረ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ ሁኔታም በተወሰኑ አመራሮች ላይም ይታይ አንደነበር አመልክተው “የትኛውም የዞንም ሆነ የወረዳ አስተዳደር የትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳደር አይመራኝም ማለት የለበትም” ብለዋል።

ስብሰባውን በማዘጋጀት የተሳተፉ የክልል ባለሥልጣናት ከሐሙስ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ እንደተናገራቸው ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሥራቸው በለቀቁ ባለሥልጣናት ምትከ “በቅርቡ” የሚተኳቸውን ሰዎቸ እንደሚመድብ ተናግረዋል።

“መሬት ላይ የገጠመንን ችግር ከመፍታተ ይልቅ እነዚህ ሰዎች መቀለ በመምጣተ ስብሰባ ለማካሄድ የፈለጉበት ዓላማ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም” ብለዋለ አቶ ጌታቸው።

ከዚሁ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመሰጠት የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ መቋቋሙ ይታወቃል።

ህወሓት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ስብሰባው በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና በሌሎችም አስተባባሪ ኮሚቴዎች ስምምነት እና ውሳኔ መሠረት የሚካሄድ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሠረት ህወሓት ለቅዳሜ እና እሁድ በመቀለ ከተማ ስብሰባ ለማካሄድ ከቀናት በፊት ጀምሮ ጥሪ እያቀረበ ሲሆን፣ ስብሰባውም በተያዘለት ጊዜ መሠረት እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ስብሰባውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያልተቀበለው ሲሆን ፕሬዝዳንቱ በስብሰባው አስተባባሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን መግለጻቸው፣ በሁለቱ ወገኖች በኩል አለመግባባት መኖሩን የሚያመለክት ነው።

የትግራይን ከ32 ዓመታት በላይ በበላይነት ሲመራ የቆየው ህወሓት ለሁለት ዓመታት በተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ከብዙ የትግራይ ተወላጆች በኩል ከባድ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን በሆኑት በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በድርጅታቸው የተጠራውን ስብሰባ አለመቀበላቸው በፓርቲው ውስጥ ችግር ሳይኖር አይቀርም የሚል ግምትን ፈጥሯል።