አሜሪካ ከኢራን የያዘችውን 1.1 ሚሊዮን ጥይቶች ለዩክሬን ሰጠች

አሜሪካ ባለፈው ዓመት ከኢራን የያዘችውን 1.1 ሚሊዮን ጥይቶች ለዩክሬን መስጠቷን ጦሯ አስታወቀ።

በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳለው ጥይቶቹ ታኅሳስ ወር ላይ ወደ የመን ሲጓዝ ከነበረ መርከብ ላይ የተወረሱ ናቸው።

በቅርቡ ዩናይትድ ኪንግደም እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የምዕራቡ የጦር ኃይሎች ዩክሬን ከሩሲያ ወረራ ራሷን እንድትከላከል የሚያቀርቡት ጥይት እያለቀባቸው እንደሆነ አስጠንቅቀው ነበር።

ማዕከላዊ ዕዙ እንዳለውም እነዚህ የኢራን ጥይቶች ሰኞ ዕለት ወደ ዩክሬን ተልከዋል።

ጥይቶቹ 'ማርዋን 1' ከተባለች ባለቤት አልባ መርከብ ላይ ታኅሳስ ወር ላይ በአሜሪካ የባህር ኃይል የተያዙ መሆናቸውንም ዕዙ ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት ሐምሌ ወር ላይ የእነዚህን ጥይቶች ባለቤትነት ያገኘውም ‘ሲቪል ፎርፌቸር’ በሚባለውና የንብረቱ ባለቤት በወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፏል ተብሎ የሚታመን ከሆነ ንብረቱ እንደሚወረስ በሚፈቅደው አሠራር ሒደት ነው።

ንብረትነቱ የኢራን የታጠቁ ኃይሎች አካል የሆነውና የአገሪቷን መንግሥት የሚጠብቀው የኢራን እስላማዊ አብዮት ጠባቂ ወታደሮች እንደሆነ ይታመናል።

ዕዙ በሰጠው መግለጫ፣አሜሪካ በቀጠናው በማንኛውም ሕጋዊ መንገድ የኢራንን የመሣሪያ ድጋፍ ለመቆጣጠር ከአጋሮቿ እና ከተባባሪዎቿ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብሏል።

በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ኢራን የሁቲ አማጺያንን ትደግፋለች ። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የ2015 ውሳኔ መሠረት ለቡድኑ መሣሪያ ማቅረብ ክልክል ነው።

በየመን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 2014 የተጀመረ ሲሆን የሁቲ አማጺያን መዲናዋን ሰንዓን ተቆጣጥረው የአገሪቷን መንግሥት አስወግደዋል።

ከሥልጣን የተወገደው መንግሥት ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሲሆን በሳዑዲ በሚመራውና በቀጠናው ባሉት አገራት ጥምረት እንዲሁም በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ይደገፋል።

ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ኢራን በዩክሬን ላለው ጦርነት ለሩሲያ መሣሪያ በተለይም ደግሞ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በማቅረብ በተደጋጋሚ ትከሳለች።

ሰኞ ዕለት ምዕራባውያኑ ለዩክሬን ስላቀረቡት ጥይቶች በዋርሶው የጸጥታ ፎረም ላይ የኔቶ ጦር ኮሚቴ ሰብሳቢ አድም ሮብ ባወር “አሁንም ቋቱ አልሞላም” ብለዋል።

ሰብሳቢው እንዳሉት በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ የኔቶ አባል አገራት የጥይት ክምችት በግማሽ ያለቀ ወይም ባዶ ነበር።

“ ለ30 ዓመታት በጋራ የገነባነው ነጻ ኢኮኖሚ ለብዙ ነገር መልካም ነው። የታጠቁ ኃይሎች ይህ የላቸውም” ብለዋል።

ጨምረውም መንግሥት እና የጦር መሣሪያ አምራቾች በከፍተኛ ሁኔታ ምርታቸውን መጨመር እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ሂፒይ የኔቶ አጋሮች የአገራቸውን ገቢ ሁለት በመቶ በመከላከያ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አባል አገራቱ በዚህ ላይ የተስማሙ ቢሆንም ከ31ዱ አባል አገራት በዚህ ዓመት ግቡን ያሳካሉ ተብሎ የሚጠበቀው11ዱ ብቻ ናቸው።