ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲ 108 አባላትን በእስር ቀጣች
ፓኪስታን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን ፓርቲ 108 አባላት በ2023 ተቃውሞ በነበራችው ተሳትፎ የእስር ፍርድ አስተላለፈች።
ግንቦት 2023 የፀጥታ ኃይሎች በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን ኢምራን ካንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተከትሎ በመላው አገሪቱ ሁከት ተቀስቅሷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የአገሪቱ ባለስልጣናት በርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ የፍርድ ውሳኔ ቢሰጡም የሐሙስ ውሳኔ ለኢምራን ካን ፒቲአይ ፓርቲ ትልቅ ጉዳት ነው።
ብይኑ የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ የሆኑት ኦማር ኤኡብ ካን ላይ የ10 ዓመት እስርን ያካትታል።
ተቃዋሚዎች ገዢው ፓርቲ በፀረ ሽብር ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን የእስር ውሳኔ ጨምሮ ስድስት የኢምራን ካሀን ፒቲአይ ሕግ አውጭዎችን ወንበራቸውን ያሳጣውን ውሳኔ አጣጥለዋል።
ፓርቲው በኤክስ ገፁ "በፓኪስታን የፍትህ ታሪክ በጣም አሳዛኝ እና አሳፋሪ ድርጊት ተፈጽሟል። በሁለቱም ምክር ቤቶች የተቃዋሚ መሪዎች የኢምራን ካን ደጋፊ፣ የሕዝብ ወኪል እና የሕገ መንግሥት ታጋይ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ተገፍተዋል" ብሏል።
ፓርቲው ብይኑን እንደማይቀበል ገልጿል።
የኢምራን ካሀን የመገናኛ ብዙኃን አማካሪ ኡሊፍ ቡኳሪ ውሳኔው "ለዲሞክራሲ ጥቁር ቀን" መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
"ተቃዋሚዎችን አንድ በአንድ መወንጀል ለየትኛውም የዲሞክራሲያው ስርዓት ጥሩ ዕድል አይደለም። ወትሮም ደካማ የሆነውን ዲሞክራሲያችንን በጣም ይጎዳል" ሲሉ ገልፀዋል።
የቀድሞው ዓለም አቀፍ የክሪኬት ስፖርት ኮከብ ኢምራን ካን ከሐምሌ 2023 ጀምሮ እስር ቤት ቢሆኑም በፓኪስታን ከፍተኛ ተወዳጅነት አላቸው።
ከሽብር ጀምሮ ብሔራዊ ሚስጥሮችን አሳልፎ በመስጠት 150 ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን እርሳቸው እና ደጋፊዎቻቸው ፖለቲካዊ ክሶች ናቸው ይላሉ።
እስራቸውን ተከትሎ በደጋፊዎቻቸው እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው መንግሥታዊ እና ወታደራዊ ተቋማትን ጥሰው ገብተዋል።
በሁከቱ ቢያንስ የ10 ተቃዋሚዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ይህም የአገሪቱ ባለሥልጣናት በካሀን ፓርቲ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ በር ከፍቷል።
በ2024 በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ በግላቸው የተወዳደሩ የፒቲአይ አባላት አብዛኞቹን ወንበሮች ቢያሸንፉም መንግሥት እንዳይመሰርቱ ግን ታግደዋል።