የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ባለቤታቸው 'ስትወለድ ወንድ ነበረች' ያለችውን አሜሪካዊት ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሰሱ

የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት እና ባለቤታቸው ብሪጂት ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ቀዳማዊት እመቤት ብሪጂት ማክሮን እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ባለቤታቸው ብሪጂት፣ አሜሪካዊቷ ተጽዕኖ ፈጣሪ ካንዴስ ኦዌንስ ቀዳማይት እመቤቷ ስትወለድ ወንድ ነበረች በማለቷ የስም ማጥፋት ክስ መሠረቱ።

በአሜሪካ ዴላዌር ግዛት ረቡዕ ዕለት የቀረበው ክስ ኦዌንስ "ያልተለመደ፣ ስም የሚያጠለሽ እና የማይመስሉ የፈጠራ ታሪኮችን" እያሠራጨች ነው ይላል።

ኦዌንስ በተደጋጋሚ በዝነኛ ፖድካስቷ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቿ ላይ ቀዳማይ እመቤቷ ስትወለድ ወንድ ነበረች የሚለውን ትናገራለች።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 ቀዳማይ እመቤቷ "በእርግጥ ወንድ ናት" የሚለው እምነቷ ትክክል መሆኑን ለማስረገጥ እስከ ዛሬ "በሙያዋ ያተረፈችውን ስም እና ዝና አደጋ ላይ እንደምትጥል" በመግለጽ ተወራርዳለች።

ኦዌንስ ረቡዕ ዕለት በተለቀቀው የፖድካስቷ ክፍል አሁንም በዚሁ አቋሟ እንደምትጸና በመግለጽ፣ክሱን "ይህ በጣም ሞኝነት ነው" ብላለች።

ኦዌንስ የፈረንሳይ ቀዳማዊት እመቤት ላይ ተሳልቃ በእርሷ መከሰሷን "ግልጽ ተስፋ የቆረጠ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ" ስትል ገልጻዋለች።

ለዓመታት የተሠራጨው የሴራ ትንተና ቀዳማይ እመቤት ብሪጂት ማክሮን ስትወለድ ወንድ እንደነበረች እና ስሟም ዣን ሚሼል ትሮግኑክስ እንደነበር ያስረዳል።

ኦዌንስ ይህንን የሴራ ትንተና ወደ 7 ሚሊየን ተከታዮች ባሉት የኤክስ ገጿ እንዲሁም በፖድካስቷ ላይ አሠራጭታለች።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ 'ብሪጂትን መሆን' የተሰኘ ተከታታይ ቪዲዮ ለቅቃለች።

ክሱን የመሠረቱት ፕሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው በጠበቆቻቸው በኩል በሰጡት መግለጫ፣ ኦዌንስ በተደጋጋሚ የምታሠራጨውን ሐሰተኛ መረጃ እንድታስተባብል መጠየቃቸውን "በመጨረሻም ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ነው" ብለው መወሰናቸውን ገልጸዋል።

"የኦዌንስ የስም ማጥፋት ዘመቻ በእኛ እና በቤተሰቦቻችን ላይ ማዋከብ እና ስቃይ ለመፍጠር እና ትኩረትን እና ታዋቂነትን ለማግኘት የተነደፈ ነው" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ገልፀዋል።

"ከእነዚህ ውንጀላዎች እንድትርቅ ሁሉንም ዕድል ሰጥተናት ነበር፤ ነገር ግን አሻፈረኝ ብላለች።"

ክሱ ኦዌንስ "የሚታወቁ የሴራ ተንታኞችን እና የተረጋገጡ ስም አጥፊዎችን መድረክን ለመደገፍ ስትል ውንጀላዋን የሚያስተባብሉ ሁሉንም ታማኝ ማስረጃዎች ችላ ብላለች" ሲል ያትታል።

በተጨማሪም ኦዌንስ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት እና ባለቤታቸው የሥጋ ዝምድና አላቸው በማለት በውሸት በመወንጀል እና ኢማኑኤል ማክሮን በሲአይኤ በምሥጢር በሥልጣን ላይ የተቀመጡ ናቸው ማለቷን በመጥቀስ ይወነጅላታል።

ኦወንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኦዌንስ ለበርካታ ወግ አጥባቂ ሚዲያዎች እና ድርጅቶች ሠርታለች

ኦዌንስ በ2024 ፖድካስትዋን ከመጀመሯ በፊት ተርኒንግ ፖይንት (Turning Point) ለተሰኘ የተማሪዎች ቡድን እና ዴይሊ ዋየር ለሚባል የወግ አጥባቂ የመገናኛ ብዙኃን ትሠራ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኮቪድ ክትባቶችን፣በአይሁዶት ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትን (ሆሎኮስት) እና ጨረቃ ላይ ስለመውጣት ካሉ ነገሮች በስተጀርባ የሚነገሩ የሴራ ትንተናዎችን እና አሉባልታዎችን ማሠራጨቷን ቀጥላለች።

ክሱ በዴላዌር በሚገኙ ድርጅቶቿ ስም የተከፈተ ሲሆን፣ መጠኑ ያልተገለጸ ጉዳት መድረሱም ሰፍሯል።

በአሜሪካ ሕግ ማክሮን እና ባለቤታቸው "የተጠቀሰውን ውንጀላ" ማረጋገጥ አለባቸው።

በዚህም የተነሳ ተከሳሿ መረጃው ውሸት መሆኑን ታውቅ ነበር፤ ነገር ግን በግዴለሽነት አትማዋለች ወይም አሠራጭታዋለች የሚለውን ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።

በመስከረም ወር ላይ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ስለ ብሪጂት ማክሮን የሐሰት መረጃዎችን አሠራጭተዋል ተብለው የተከሰሱ ሁለት ሴቶችን በስም ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ነገር ግን ይህ ውሳኔ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ይግባኝ ቀርቦበት መቀልበሱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።