ማክሮን በአደባባይ የተገፈተሩት 'ለቀልድ' እንጂ የቤት ውስጥ ጸብ አይደለም አሉ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለጉብኝት ቬትናም ዋና ከተማ ሃኖይ አውሮፕላን ማረፊ ደርሰው ከአውሮፕላን ሊወርዱ ሲሉ የሆነው በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ሆኗል።
የአውሮፕላኑ በር ተከፍቶ ፕሬዝዳንቱ ፊት ለፊት በሚታዩበት ጊዜ አንድ እጅ ጸብ በሚመስል ሁኔታ ፊታቸውን በኃይል ሲገፋ ታይቷል። በዚህ ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ምንም እንዳልተፈጠረ የእጅ ሰላምታ ሰጥተው ሚስታቸውን ከጎናቸው በማድረግ ከአውሮፕላኑ ወርደዋል።
እሁድ ምሽት በፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን ውስጥ የማክሮን ሚስት ብሪጂት ፊታቸው ሳይታይ ከአውሮፕላኑ በር በጎን በኩል ሆነው በእጃቸው የማክሮንን ፊት በኃይል ሲገፈትሩ የተቀረጸው ምሥል በጥንዶቹ መካከል የተፈጠረ ጸብ እንዳለ እየተነገረ ነው።
ፕሬዝዳንት ማክሮን በድንገት በገጠማቸው ነገር መጀመሪያ ላይ የደነገጡ ቢሆንም ወዲያ ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ከአውሮፕላኑ ውጪ ሊቀበኋቸው ለተሰበሰቡት የቬትናም ባለሥልጣናት እና ካሜራ ደግነው ለሚጠብቋቸው ጋዜጠኞች የእጅ ሰላምታ ሰጥው ነበር።
ነገር ግን ምሥሉ ከተሠራጨ በኋላ ማክሮን በሚስታቸው ሲመናጨቁ እና ሲገፈተሩ በድንገት በሕዝብ ፊት መታየታቸውን በመጥቀስ ጉዳዩ በጥንዶቹ መካከል የተፈጠረ ጠንከር ያለ ችግር ሳይኖር አይቀርም ተብሏል።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን የፕሬዝዳንቱን ቤተ መንግሥት ኤሊሴ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ክስተቱ ፕሬዚዳንቱ እና ባለቤታቸው መካከል የመቀላለድ ሁኔታ ነው ሲሉ፤ ማክሮንም በበኩላቸው እየተቀላለዱ ሳለ መታየታቸውን በመግለጽ አስተባብለዋል።



