ሕንድ በአሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪ እና ሥራ ፈጣሪ ዜጎቿን መመለስ ትችል ይሆን?

የህንድን ሰንደቅ ኣላማ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠበቅ ያለው አሜሪካ የስደተኛ ፖሊስ ህንዳዊኣን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየገፋፋ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በልዩ ሙያዎች ለሥራ ቅጥር የሚሰጠውን 'ኤች-1ቢ' ቪዛ ክፍያ ሳይታሰብ 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ማድረጋቸው የዴልሂ ፖሊሲ አውጭዎች ዜጎቻቸውን ለመመለስ ውትወታ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በቅርበት የሚሰሩ አንድ ሹም መንግሥት በውጭ የሚገኙ ሕንዳውያን እንዲመለሱ እና ለአገር ግንባታ እንዲያበርክቱ በቅርበት እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምጣኔ-ሀብት ምክር ቤት አባል ደግሞ 'ኤች-1ቢ' ሁሌም ቢሆን ለተቀባዩ አገር ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ የክፍያ ጭማሪው ሕንድ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ለመሳብ ያን ያህል አይጠቅምም ብለዋል።

የክርክሩ ዋነኛ ሀሳብ ሕንድ በቴክኖሎጂ፣ በሕክምና እና በሌሎች የፈጠራ ኢንዱስትሪው አገራቸውን ባለፉት 30 ዓመታት ለቀው የወጡ ዜጎቿን ወደ እናት አገራቸው መመለስ ላይ ያጠነጥናል።

ለስደተኞች በአሜሪካ ያለው አዋኪ ከባቢ አንዳንድ ሕንዳውያን ምርጫቸውን ዳግም እንዲያጠኑ አስገድዷል።

ይሁን እንጂ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሕንዳዊያንን አሜሪካን ጥለው እንዲመጡ መፈለግ መናገሩ ብቻ እንደሚቀል በርካታ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኒቲን ሀሰን በአሜሪካ ሜታ ኩባንያ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ደሞዙን ሥራውን በመልቀቅ ወደ ሕንድ ተመልሷል

የፎቶው ባለመብት, Nithin Hassan

የምስሉ መግለጫ, ኒቲን ሀሰን በአሜሪካ ሜታ ኩባንያ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ደሞዙን ሥራውን በመልቀቅ ወደ ሕንድ ተመልሷል

ኒቲን ሀሰን ባለፉት 20 ዓመታት አሜሪካ ኑሯቸውን ከመሠረቱ ሕንዳዊያን መካከል የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት የሕንድ ሲሊኮን ቫሊ ወደ ሚባለው ባንጋሉሩ ሲዘዋወር ተስፋን አዝሎ ነበር።

ቀላል ውሳኔ አልነበረም። ሚሊዮን ዶላሮችን ይከፍለው ከነበረው ሜታ ኩባንያ ያልተጨበጠ የሥራ ፈጠራ (ስታርት አፕ) ዓለምን ለመቀላቀል ነበር ሥራውን የለቀቀው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ሁሌም ቢሆን የራሴን ነገር ለመፍጠር ፍላጎት ነበረኝ። ነገር ግን በአሜሪካ የስደተኛነት ሁኔታዬ ይህን ነፃነቴን ገድቦታል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኒቲን ከተመለሰ በኋላ 'ባክ ቱ ኢንዲያ' የተሰኘ አሜሪካ ያሉ ሌሎች ሕንዳዊያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የሚያስረዳ መድረክን ጨምሮ ሁለት አዲስ ሥራዎችን (ስታርት አፖችን) ጀምሯል።

በቅርብ ወራት የአሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲ መቀየር ሰዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ መረጃ የሚያፈላልጉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ እና 'ኤች-1ቢ' ቪዛ ክፍያ መጨመር ይህን አዝማሚያ ከፍ እንደሚያደርገው ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በርካታ ባለሙያዎች አሁን 'ግሪን ካርድ' ላያገኙ እንደሚችሉ አምነዋል። እና 'ቢ2አይ' [የአጭር ጊዜ ቪዛ] ጥያቄ ጨምሯል፤ ከትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን በኋላ በሦስት እጥፍ ገደማ ጨምሯል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ200 የሚበልጡ ሕንዳዊያን ለመመለስ ያሏቸውን አማራጭ ለማወቅ ግንኙነት አድርገዋል"።

ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ሕንዳውያንን ለሥራ የሚመለምሉ ሙያተኛ አፈላላጊ ሰዎች የተቀየረውን አዝማሚያ ደግፈው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

'ቢዲኦ' የተባለ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሻቪኒ ዳሲያ "በስመ ጥር የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ እና ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ሕንዳውያን ተማሪዎች በዚህ ወቅት በ30 በመቶ ጨምሯል" ይላሉ።

እርግጠኛ አለመሆን ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑ ሕንዳዊያንንም በአሜሪካ ስለሚኖራቸው የሥራ ሕይወት ዳግም እንዲያጤኑ መገፋፋቱንም አክለው ተናግረዋለል።

ለዚህ ግዙፍ የአስተሳሰብ ለውጥ ባለፉት ዓመታት በሕንድ የተከፈቱት እና ለተመላሽ ሕንዳውያን የሥራ እድል እየሰጡ ያሉ ኩባንያዎችም ሌላኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

አሜሪካ በሯን የምትዘጋ ከሆነ እነዚህ ቢሮዎች በቴክኖሎጂ ኢንደስትሪው ላሉ ሕንዳዊያን ማረፊያ ለሆኑ የሚችሉ ሲሆን፤ የሰው ሀብት አስተዳደር ድርጅት የሆነው ፍራንክሊን ቴምፐልተን ቢሮዎቹ በተለይም በሌሎች አገራት የቀነሰውን የሥራ ዕድል ይስባሉ ብሏል።

ትራምፕ 'ኤች-1ቢ' ቪዛን ጠበቅ ሲያደርጉ እንደ ጀርመን ያሉ አገራት የህንድን የሰለጠኑ ሠራተኞች ለመቀበል በራቸው ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ 'ኤች-1ቢ' ቪዛን ጠበቅ ሲያደርጉ እንደ ጀርመን ያሉ አገራት የህንድን የሰለጠኑ ሠራተኞች ለመቀበል በራቸው ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል

ይሁን እንጂ ስደትን በሆነ ደረጃ ያህል ለመቀልበስ መንግሥት ተጨባጭ እና ጠንከር ያለ ጥረት ማድረግ ያስፈልገዋል፤ ይህ አሁን የለም ይላሉ የመገናኛ ብዙኃን አማካሪ እና ፀሐፊ ሆኑት ሳንጃይ ባሩ።

"መንግሥት መመለስ የሚፈልጋቸውን ጎበዝ ተመራማሪዎችን፣ ሙያተኞችን እና ሥራ ፈጣሪዎችን ጨምሮ ግለሰቦችን ወጣ ብሎ መለየት ይኖርበታል። ጥረት ይፈልጋል፤ እና ከላይ መወሰን አለበት" ይላሉ።

የሕንድ መጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋኸርላ ንህሩ በኅዋ እና ኒውክሌር ቴክኖሎጂ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን ለመመለስ እና ተቋማትን ለመገንባት ይህን እንዳደረጉም ያነሳሉ።

"በጠንካራ ዓላማ እና አገራዊ ስሜት ተገፋፍተው ነበር። አሁን ለመመለስ ማበረታቸው ምንድን ነው?" ሲሉም ሳንጃይ ባሩ ይጠይቃሉ።

በሙያቸው ለዓመታት የሰለጠኑ ሙያተኞች አገሪቱን በገፍ ለመልቀቃቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ገፊ ምክንያቶች አሉ የሚሉም ሲሆን፤ ህንድ ይህን ከመቆጣጠር ይልቅ በደስታ ትመለከተዋለች ይላሉ።

አሜሪካ 'ኤች-1ቢ' ቪዛን ጠበቅ ስታደርግ እንደ ጀርመን ያሉ አገራት ደግሞ የሕንድን የሰለጠኑ ሠራተኞች ለመቀበል ቀይ ምንጣፍ ዘርግተዋል።

ሕንዳዊያን ሙያተኞች በርካታ ባለሀብቶችን እና ተከፋይ ሕንዳውያንን ባለፉት ዓመታት ያባረረው ደካማ የቁጥጥር ስርዓት፣ አድካሚ ቢሮክራሲ እና ሥራ ለመስራት ምቹ ያልሀነ ከባቢ እንደሚያስቸግራቸው እሙን ነው።

ከ2020 ወዲህ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕንዳውያን ዜግነታቸውን መቀየራቸውን የመንግሥት መረጃ ያሳያል።

ኒቲን ሀሰን መንግሥት ሙያተኞችን ለመመለስ ቁርጠኛ ከሆነ አሳሪ ሁኔታዎችን አንድ ላይ ለመፍታት መስራት እንዳለበት ይናገራል።

ይህም የታክስ ሕግን ቀለል ማድረግ፣ የአዲስ ሥራ ማበረታቻዎች እና ሌሎች እንደ መሠረተ ልማት እና የከተማ መጨናነቅ የመሰሉ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታትን ያካትታል።

ይህም ማለት የምርምር እና ልማት ማዕከሎችን ማሳደግ እና የአገር ውስጥ ትምህርትን ማሳደግን ጨምሮ የተማሩ ዜጎች ስኬታማ እንዲሆኑ የተሻለ የሥራ ከባቢ መፍጠር መሆኑን ሳንጃይ ባሩ ይናገራሉ።

ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ለሕንዳዊያን ባለሙያዎች አሜሪካን ሳቢ እንድትሆን ያደረጉ ጉዳዮች በሕንድም ሊፈጠሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።