ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 22 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገለጸ
እስራኤል በሰሜን እና በማዕከላዊ ጋዛ በፈጸመቻቸው ተከታታይ የአየር ድብደባዎች ቢያንስ 22 ፍልስጤማውያን መገደላቸው የሕክምና እና የሲቪል መከላከያ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የመኖሪያ በቶችን ጨምሮ አምስት ቦታዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን ተናግረዋል። ከሟቾቹ መካከል የሐማስ ከፍተኛ አዛዥ እንደሚገኙበት የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት በጋዛ ኢላማዎችን መምታቱን የገለጸ ሲሆን፣ አንድ "አሸባሪ ታጣቂ" በእስራኤል ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያሉ ቦታዎችን የሚለይ እና "ቢጫ መስመር" የሚል ስያሜ የተሰጠውን የሰርጡን መስመር አቋርጦ በወታደሮች ላይ በመተኮሱ የተሰጠ የአጸፋ ምላሽ ነው ብሏል። ሐማስ ይህንን አስተባብሏል።
ሁለቱም ወገኖች ከስድስት ሳምንታት በፊት የተፈራረሙበትን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ እርስ በእርስ ይካሰሳሉ።
በጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ከ310 በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃቶች ተገድለዋል።
የአካባቢው የሲቪል መከላከያ እንዳስታወቀው ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጥቃት በሰሜን የምትገኘውን የጋዛ ከተማ እንዲሁም በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘውን የዴይር አል-ባላህን እና የኑሲራት ካምፕን ኢላማ አድርጓል።
የሐማስ ባለሥልጣናት በጋዛ ከተማ በርካታ ሕዝብ በሚኖርበት የሪማል አካባቢ በሚገኘው እና አባስ የሚል ስያሜ ባለው መስቀለኛ መንገድ ላይ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። የዐይን እማኞች የእስራኤል ጥቃት መኪና አቃጥሏል ብለዋል።
በተጨማሪም በዴር አል-ባላህ በሚገኝ መስጊድ አቅራቢያ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
በኑሴራት የተፈጸሙ የእስራኤል ጥቃቶች ሁለት ቤቶችን ዒላማ ያደረጉ መሆናቸውን እና የአቡ አሙኔህ ቤተሰብ ቤት ከተመታ በኋላ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን አክለዋል። በአቡ ሻዊሽ ቤተሰብ መኖሪያ ላይ በተደረገ ሌላ ጥቃት ሌሎች ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።
ቅዳሜ ዕለት በምዕራብ ጋዛ ከተማ የአንድ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንንሚን ኔታንያሁ ቢሮ ባወጣው መግለጫ "ዛሬ ሐማስ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን ለማጥቃት አሸባሪ ወደ እስራኤል ይዞታ ግዛት በመላክ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደገና ጥሷል። በምላሹም እስራኤል አምስት ከፍተኛ የሐማስ አሸባሪዎችን አስወገዳለች" ብሏል።
መግለጫው አሸማጋዮች "ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲፈጽም አጥብቀው እንዲጠይቁ" ጥሪ አቅርቧል።
ከጥቃቶቹ በኋላ ሐማስ ጦሩ በምዕራብ በኩል ቢጫ መስመሩን መግፋቱ እና የምሥራቅ ጋዛን የቦምብ ድብደባ መቀጠሉ የስምምነቱን "በግልጽ መጣስ" እንደሆነ ተናግሯል።
ቡድኑ እስራኤል "አዲስ እውነታዎችን መሬት ላይ ለመጫን" እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማዳከም እየሞከረች መሆኑን በማስጠንቀቅ አሸማጋዮች እና አሜሪካ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።
በጋዛ በእስራኤል በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ 69,500 ሰዎች ተገድለዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ 280 የሚሆኑት በተኩስ አቁም ወቅት የተገደሉ መሆናቸውን የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።