ደቡብ አፍሪካ 'ከአገራቸው ማጽዳት ነው' በማለት ፍልስጤማውያንን እንደማትቀበል አስታወቀች

ከጋዛ የመጡ ናቸው የተባሉ በርካታ ፍልስጤማውያን ወደ ግዛቷ መግባታቸውን ተከትሎ አገራቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የሚያደርጉ ፍልስጤማውያንን ከዚህ በኋላ እንደማትቀበል አስታወቀች።

ፍልስጤማውያኑ በብዛት ከአገራቸው እንዲወጡ የሚደረግ "የማጽዳት አጀንዳ" ሊሆን ይችላል በማለት ከጋዛም ሆነ ከሌሎች ግዛት የሚመጡ ፍልስጤማውያንን አስጠንቅቃለች።

ደቡብ አፍሪካ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ባለፈው ሳምንት ከጋዛ ወደ አገሪቱ 153 ፍልስጤማውያን ተሳፋሪዎችን የያዘ አውሮፕላን አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ወደ ግዛቷ ከገቡ በኋላ ነው።

ከ150 በላይ የሚሆኑት በአንድ አውሮፕላን የተሳፈሩ ፍልስጤማውያን ደቡብ አፍሪካ መድረሳቸው ብዙ ገጽታዎቹ ግልጽ ያልሆነ እና አከራካሪ ሆነው እንደተገኙ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በዚህም ምክንያት ደቡብ አፍሪካ ከዚህ በኋላ ፍልስጤማውያንን የሚያጓጉዙ ተጨማሪ የቻርተር በረራዎችን መቀበል እንደማትፈልግ ገልጻለች።

በረራው "ፍልስጤማውያንን ከጋዛ እና ከዌስት ባንክ የማጽዳት ግልጽ አጀንዳ" አካል ነበር ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሮናልድ ላሞላ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ለዚህ ክስ ምላሽ አልሰጡም። ሆኖም ደቡብ አፍሪካ ቀደም ሲል 153ቱን ፍልስጤማውያን ለመቀበል ተስማምታ እንደነበር ተናግረዋል።

ቢቢሲ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የፍልስጤም ኤምባሲ ቡድኑ ከእስራኤልን ራሞን አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ አገሪቱ "ምንም ዓይነት መልዕክት ቀድሞ ሳይላክ እና ያለምንም ቅንጅት" በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በኩል እንደበረረ ተናግሯል።

"ያልተመዘገበ እና አሳሳች ድርጅት" የጋዛ ዜጎችን ችግር እንደተጠቀመበት፣ "ቤተሰቦችን እንዳታለለ፣ ገንዘብ እንደሰበሰበ እና መደበኛ ባልሆነ እና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ጉዟቸውን እንዳመቻቸ" ተናግሯል።

የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤምባሲው በኩል "ከዚህ ውድቀት የተነሳ ይህንን ሁኔታ ለመፍታት" ከደቡብ አፍሪካ ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግሯል።

ለዚህ ውዝግ መንስዔ የሆነው በረራ በደቡብ አፍሪካ ኦአር ታምቦ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሰው ሐሙስ ዕለት ነበር።

ተሳፋሪዎቹ መጀመሪያ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳይገቡ በመከልከላቸው ከአስር ሰዓታት በላይ ከአውሮፕላኑ መውረድ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ በተደረገው ጦርነት የፍልስጤምን ዓላማ በፅኑ የደገፉት የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ይህ የሆነው ተሳፋሪዎቹ በፓስፖርታቸው ውስጥ የመነሻ ማህተሞች ስላልነበሯቸው ነው።

ፍልስጤማውያን ያለ ቪዛ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲጓዙ እና ለ90 ቀናት እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል።

በመጨረሻም ተሳፋሪዎቹ በደቡብ አፍሪካ የሚንቀሳቀስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጣልቃ ከገባ በኋላ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተፈቅዶላቸዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ይህ የሆነው "ከርህራሄ እና ሐዘኔታ" የተነሳ ነው ብለዋል።

ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ ሃያ ሦስቱ ተሳፋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ስለበረሩ የተቀሩት ፍልስጤማውያን ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄደው የቡድን 20 መሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ የደቡብ አፍሪካን ዝግጁነት በተለመከተ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላሞላ የሐሙስ ዕለቱ በረራ "ፍልስጤማውያንን ከፍልስጤም ወደ ብዙ የዓለም ክፍሎች የማስወገድ ሰፊ አጀንዳ" አካል እንደሆነ ተናግረዋል።

"[ይህ] በግልጽ የተቀናበረ ተግባር ነው፤ ምክንያቱም ወደ ደቡብ አፍሪካ ብቻ አይደለም የተላኩት። እንደዚህ ዓይነት በረራዎች የተላኩባቸው ሌሎች አገራትም አሉ" ሲሉ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ተናግረዋል። ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንም አክለዋል።

'ጊፍት ኦፍ ዘ ጊፍትስ' የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደገለጸው ከሁለት ሳምንታት በፊት 176 ፍልስጤማውያንን የያዘ ሌላ አውሮፕላን በጆሃንስበርግ ያረፈ ሲሆን፣ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ወደ ሌሎች አገራት ሄደዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ "በፈቃደኝነት" ወደ ሌሎች አካባቢዎች ስለማስፈር በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ይህ እርምጃ በፍልስጤማውያን፣ በሰብአዊ መብት ቡድኖች እና በብዙ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተተቸ ነው።

ከበረራው አንድ ቀን በኋላ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ፍልስጤማውያን "በናይሮቢ በኩል ባለፈ አውሮፕላን ውስጥ በሆነ መንገድ ተጭነው ወደ ደቡብ አፍሪካ በረሩ" ማለታቸውን ኒውስ24 ዘግቧል።

የጋዛን መተላለፊያዎችን የሚቆጣጠረው የእስራኤል ጦር አካል ኮጋት ባወጣው መግለጫ "ነዋሪዎቹ ጋዛ ሰርጥን ለቅቀው የወጡት ኮጋት ከሚቀበላቸው ሦስተኛ አገር ፈቃድ ካገኘ በኋላ ነው" ብሏል። ነገር ግን በወቅቱ ተቀባይ የተባለው አገር አልገለጸም።

ኮጋት ሰኞ ዕለት ደቡብ አፍሪካን ፍልስጤማውያንን ለመቀበል የተስማማች ሦስተኛ አገር መሆኗን ጠቅሷል።

ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ትቃወማለች።

አገሪቱ ፍልስጤማውያን ለነጻ አገርነት የሚያደርጉትን ትግል የምትደግፈው ከአስርተ ዓመታት በፊት ጀምራ ሲሆን፣ በተለይም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የፀረ-አፓርታይድ ተምሳሌት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ለፍልስጤማውያን ዓላማ ድጋፍ ለመስጠት የገቡት ቃል ይታወሳል።

ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በደቡብ አፍሪካ ዙሪያ ትላልቅ ለፍልስጤም ድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ትልቁን የአይሁድ ማኅበረሰብ የሚያስተናግድ አነስተኛ የእስራኤል ደጋፊ ሰልፎችም ተካሂደዋል።

በ2023 የደቡብ አፍሪካ መንግሥት እስራኤልን በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በማለት ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቧል።

እስራኤል የደቡብ አፍሪካን ጥያቄ "መሠረተ ቢስ" በማለት አጥብቃ ውድቅ አድርጋዋለች።