"ሙዚቃ ካለ ቀዶ ሕክምና ቀላል ይሆናል፤ ታካሚዎችም በፍጥነት ያገግማሉ"- ጥናት

በሕንድ መዲና ደልሒ በሚገኝ ሆስፒታል የሐሞት ከረጢት ቀዶ ሕክምና እየተካሄደ ነው። ታካሚዋ ማደንዘዣ ተሰጥቷት አልጋ ላይ ተኝታለች።

ሐኪሞች ለቀዶ ሕክምናው እየተዘጋጁ ነው። ታካሚዋ በጆሮዋ ሄድፎን አድርጋ ለስላሳ የዋሽንት ሙዚቃ ተከፍቶላታል።

ማደንዘዣው የሰውነቷን እና የአብዛኛውን የአንጎሏን ክፍል ሥራ ቢገታም፤ ድምጽ የሚያስተጋባበት የጆሮዋ ክፍል ሙሉ በሙሉ አልተዘጋም።

ሙዚቃ ሳይሰሙ ቀዶ ሕክምና ለሚደረግላቸው ታካሚዎች እንደ ፕሮፖፎል እና ኦፒዮይድ ያሉ ጠንካራ ማደንዘዣዎች ይሰጧቸዋል።

ለደልሒዋ ታካሚ እነዚህ ማደንዘዣዎች ስላልተሰጧት ከገባችበት ሰመመን ለመንቃት አጭር ጊዜ ይወስድባታል።

በደልሒ ማሉና አዚድ ሜዲካል ኮሌጅ የተሠራው ጥናት፤ እነዚህ የማደንዘዣ መድኃኒቶች ሙዚቃ ለሚሰሙ ታካሚዎች እንደማይሰጡ ይጠቁማል።

'ሚውዚክ ኤንድ ሜድስን' የተባለው መጽሔት ላይ የታተመው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ማደንዘዣ በሚሰጥበት ወቅት ታካሚዎች ሙዚቃ የሚሰሙ ከሆነ የሚሰጣቸውን የማደንዘዣ መጠን መቀነስ ይቻላል።

ታካሚዎቹ ሙዚቃ መስማታቸው በፍጥነት እንዲያገግሙም ይረዳል።

ምርምሩ በዋነኛነት ያተኮረው የሐሞት ከረጢት ላይ በሚደረግ ቀዶ ሕክምና ነው።

ቀዶ ሕክምናው ከአንድ ሰዓት በታች ይጠናቀቃል።

የማደንዘዣ መድኃኒት እና የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ፋራሕ ሑሴን እንደሚሉት የጥናቱ ዋነኛ ግብ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ ቶሎ ከሆስፒታል እንዲወጡ ማድረግ ነው።

"ቀዶ ሕክምናው ተጠናቆ ታካሚዎች ከሰመመን ሲወጡ አእምሯቸው ንቁ መሆን አለበት። ሕመም ሊሰማቸውም አይገባም" ይላሉ ባለሙያው።

ይሄንን ለማሳካት አምስት ወይም ስድስት መድኃኒቶች በጥንቃቄ ይቀመማሉ።

እነዚህ መድኃኒቶች ታካሚዎችን የሚያስተኙ፣ ሕመምን የሚገቱ፣ ጡንቻ ውስጥ የሚቀረውን የቀዶ ሕክምና ትውስታ የሚያስረሱ እና ጡንቻን የሚያፍታቱ ናቸው።

የሐሞት ከረጢት ቀዶ ሕክምና (laparoscopic gallbladder removal) የሆድ ግድግዳ ነርቮችን የሚያደነዝዝ መድኃኒት ያስፈልገዋል።

አጠቃላይ ማደንዘዣ (General anesthesia) ሰውነት ሕመም እንዳይሰማው እንደሚያደርግ ከጥናቱ ተመራማሪዎች አንዱ ዶ/ር ታናቪ ጎል ይናገራሉ።

ማደንዘዣ ቢኖርም ቀዶ ሕክምና ለሰውነት ከባድ ነው። የልብ ምት፣ ሆርሞን እና የደም ግፊት ይጨምራል።

ዶ/ር ፋራሕ እንደሚሉት ሰውነት በቀዶ ሕክምና ጭንቅ ውስጥ ሲገባ የሚሰጠው ምላሽ የማገገም ሒደትን ያዘገያል።

ሰውነት ላይ የሚፈጠረው ጫና ቀዶ ሕክምናው ሲጀመር ካለው የሰውነት መቀደድ ወይም ሰውነት ውስጥ አየር እንዲዘዋወር ከሚረዳው የመተንፈሻ ትቦ ሊመነጭ ይችላል።

ማደንዘዣ የሚሰጡ ሐኪሞች በጉሮሮ ሥር ያለውን ለስላሳ ሕዋስ በማንሳት በቀጥታ ወደ ድምጽ ሳጥን ያመራሉ። አየር በቀላሉ ወደ ሰውነት እንዲገባ የሚያስችል መንገድ ሲሆን፤ ሰመመን ውስጥ ያሉ ታካሚዎች እንዲተነፍሱ ይረዳል።

በጉሮሮ ሥር ያለውን ለስላሳ ሕዋስ ማንሳት (laryngoscopy) እና መተንፈሻ ትቦውን ወደ ሰውነት የማስገባት ሒደት (intubation) ለሰውነት ከባድ መሆኑን ዶ/ር ሶኒያ ዋድዋን ይናገራሉ።

በሙላና አዛድ ሜዲካል ኮሌጅ የማደንዘዣ እና ጽኑ ሕሙማን ክፍል ባለሙያዋ ዶ/ር ሶኒያ እንደሚሉት፤ ሰዎች በሰመመን ውስጥ ሆነውም ሰውነታቸው መጨነቁ አይቀርም።

ከፍተኛ የማደንዘዝ አቅም ያለው ፕሮፖፎል ጥቅም ላይ የሚውለውም ለዚህ ነው። በ12 ሰከንዶች ታካሚዎች ሰመመን ውስጥ ይገባሉ።

ታካሚዎችን ለማደንዘዝ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ፕሮፖፎል እና ፌንታኔል መጠን ለመቀነስ ሙዚቃ ላይ ምርምር አድርገዋል።

የማደንዘዣ መጠን ሲቀነስ ታካሚዎች በፍጥነት ከሰመመን ይነቃሉ፤ ሰውነታቸው በተሻለ ሁኔታ ይሠራል፤ የሚደርስባቸውን የጎንዮሽ ጉዳትም መቀነስ ይቻላል።

ከ20 እስከ 45 ዓመት የሆናቸው 56 አዋቂዎች ላይ 11 ወራት የወሰደ ምርምር ተደርጓል።

ታካሚዎቹ ድምጽ የማያስገባ ሄድፎን አድርገው፣ ማደንዘዣ መድኃኒት ተሰጥቷቸው ነው ጥናቱ የተሠራው።

ከፒያኖ እና ከዋሽንት ሙዚቃ አንዱን እንዲመርጡ ተጠይቀዋል።

"ሰውነት ሰመመን ውስጥ ቢሆንም ሥራውን የሚቀጥል የአንጎል ክፍል አለ። ታካሚዎቹ ሙዚቃውን መስማታቸውን ላያስታውሱ ይችላሉ። ግን በፍጥነት እንዲያገግሙ ይረዳቸዋል" ሲሉ ዶ/ር ፋራሕ ያስረዳሉ።

ሙዚቃ እየሰሙ የታከሙ ሰዎች የተሰጣቸው ፕሮፖፎል እና ፌንታኔል ውስን ነው። በቶሎ ከማገገማቸው ባሻገር ሰውነት በጭንቀት ወቅት የሚለቀው ሆርሞን (cortisol) መጠናቸው አነስተኛ ሆኗል።

"ሰመመን ውስጥ ሙዚቃ የመስማት ዕድል ጠባብ ቢሆንም ሙዚቃ የአእምሮ አሠራር ላይ ለውጥ ያሳያል። ሙዚቃውን ታካሚዎች ቢረሱትም አእምሮ ያስታውሰዋል" ይላሉ ተመራማሪው።

ቀዶ ሕክምና ሲደረግላቸው በሰመመን ውስጥ ሆነውም የተወሰነ ትውስታ ያሳዩ ታካሚዎች አሉ። ሰውነታቸው አሉታዊ ተሞክሮን ያስታውሳል።

ሙዚቃ ተሞክሯቸውን አወንታዊ ስለሚያደርገው ትውስታቸው የተሻለ እንደሚሆን ጥናቱ ያሳያል።

"ሙዚቃ በአእምሮ ላይ ያለውን ሚና ገና እያጠናን ነው። ቀዶ ሕክምና ክፍልን ሰዋዊ መልክ ማላበስ እንሻለን" ይላሉ ዶ/ር ፋራሕ።

እንደ ስትሮክ ያሉ ሕመሞችን ለማከም ሙዚቃ ጥቅም ላይ ይውላል። የሙዚቃ ውጤታማነት ላይ ተጨማሪ ምርምሮች ሲካሄዱ ቀዶ ሕክምና የሚከናወንበት መንገድ እስከወዲያኛው ይለወጥ ይሆናል።