ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች 100 ሺህ ዶላር እንዲያስይዙ የምትጠይቀው አፍሪካዊት አገር
በመጪው ታኅሣሥ በጊኒ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዕጩነት የሚቀርቡ ተፎካካሪዎች አንድ መቶ ሺህ ዶላር ማስያዣ ማቅረብ እንዳለባቸው መገለጹ የአገሪቱን ዜጎች ግራ አጋብቷል።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ይዘው ባለፉት አራት ዓመታት ጊኒን በወታደራዊ መሪነት ያስተዳደሩት ኮሎኔል ማማዱ ዱምቡያ ሥልጣናቸውን በሕዝብ ለሚመረጥ ሲቪል መንግሥት ለማስረከብ ተዘጋጅተዋል።
የአሁኑ ምርጫ አዲስ በተዘጋጀው ሕገመንግሥት መሠረት የሚካሄድ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ወታደራዊው መሪ በምርጫው እንደሚሳተፉ ባያሳውቁም ሕጉ መወዳደር እንዲችሉ ፈቅዶላቸዋል።
ቀደም ሲል በነበሩት ምርጫዎችም ዕጩዎች ገንዘብ ማስያዝ የሚጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም የአሁኑ ግን ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ተንታኞች በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የቆየው ወታደራዊ መንግሥት በምርጫ አስተዳደሩን በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት ለማስረከብ በሚያካሂደው ታሪካዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በዕጩነት ከመቅረብ እንዲያፈገፍጉ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።
"ይህ የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ነው" በማለት የፖለቲካ ተንታኙ ካቢኔት ፎፋና ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ይህ ውሳኔም በአጠቃላይ የምርጫው ሂደት ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ትችት ያባብሰዋል" ብለዋል።
ዕጩዎች የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ አስይዘው በምርጫው ውስጥ ከተሳተፉ በኋላ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከአምስት በመቶ በላይ የሚሆን የመራጮች ድምጽ ካገኙ ገንዘባቸው ተመላሽ ይደረግላቸዋል።
የጊኒ የምርጫ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ዕጩዎች ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያሲይዙ የተደረገው ተአማኒ ዕጩዎች ብቻ በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው።
በዚህ ምርጫ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ፋያ ሚሊሞኖ ቀደም ሲል በአገሪቱ በተካሄዱት ምርጫዎች የሚቀርበው የማስያዣ ገንዘብ መጠን ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
"አስከ 2005 (እአአ) ድረስ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ማስያዣው ዝቅተኛ ነበር። እብደቱ የጀመረው በ2010 የተወሰኑ ዕጩዎችን ከምርጫው ለማስወጣት በታሰበበት ጊዜ ነበር። አሁን ደግሞ የበለጠ አድጎ ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር ተደርጓል።"
ጊኒ በምትገኝበት በአንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ በምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከፍተኛ ነው።
በ2022 የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ተወዳዳሪ ዕጩዎች በምርጫ ለመሳተፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲያስይዙ በማድረጉ ከፍተኛ ትችት አስነስቶበት ነበር።
በተመሳሳይ የምርጫ ተፎካካሪ ዕጩዎች በካሜሩን 53 ሺህ ዶላር እንዲሁም በአይቮሪ ስኮስ 90 ሺህ ዶላር እንዲያስይዙ ይጠበቅባቸዋል።
ጊኒ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ዕጩዎች ከሚያስይዙት ገንዘብ በተጨማሪ በምርጫ ዘመቻው ወቅት የሚያወጡት ገንዘብ መጠን አንድ ዕጩ ከ4.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳያደርግ የምርጫ አስፈጻሚው አካል ገደብ ጥሏል።
አንድ በምርጫው የሚሳተፍ ዕጩ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማስያዣ "በጣም ሀብታም የሆኑ ወይም ከመንግሥት ሀብት ተጠቃሚ የሆኑት ብቻ የሚወዳደሩበት እንደሆነ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው" ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
አስካሁን ወደ 50 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች እና 16 የግል ዕጩዎች የሚጠበቅባቸውን አሟልተው በምርጫው በዕጩነት ለመቅረብ ተቀባይነት አግኝተዋል።
ምንም እንኳን አሁንም ጊዜ ቢኖራቸውም በአገሪቱ ያሉት ሦስቱ የታላላቆቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በምርጫው ላይ ዕጩ ሆነው ስለመቅረባቸው የታወቀ ነገር የለም።
ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ከጊኒ ውጪ በሌላ አገር ውስጥ ነው።