የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛው የህወሓት ክንፍ ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አለው ሲል ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, EBC
የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛው የህወሓት ክንፍ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እና ትብብር አለው በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሰ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ይህንን ያሉት አርብ አዲስ አበባ ውስጥ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በክልሉ ስላለው ሁኔታ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ነው።
ሚኒስትሩ ይህንን እና ሌሎችንም ክሶች በህወሓት አንደኛው ወገን ላይ ባቀረቡበት ጊዜ ግንኙነቱ ከየትኛው የውጭ ኃይል ጋር እየተደረገ መሆኑን በስም አልጠቀሱም።
በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት በተባባሰበት ባለፉት ወራት በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት አንጃ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረገ መሆኑን ተጠቅሶ በተደጋጋሚ ሲከሰስ ቆይቷል።
አቶ ጌታቸው ረዳም ከዚህ ቀደም በሰጡት መግለጫ ላይ አንዳንድ የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረጉ ናቸው ሲሉ መክሰሳቸው ይታወቃል።
በደብረ ፂዮን የሚመራው ቡድን ግን እየቀረበበት ያለውን ይህንን ክስ በተደጋጋሚ እያስተባበለ ይገኛል።
ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑት ዲፕሎማቶች በተሰጠው ማብራሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛው የህወሓት ክንፍ ከውጭ ኃይል ጋር ግንኙነት ከመፍጠር በተጨማሪ "ግጭት ለመቀስቀስ ሙከራ እያደረገ ነው" ተብሎ ተወቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መንግሥታቸው በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወቅታቂ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አመለክተው፤ አንደኛው የህወሓት ክንፍ "ጊዜያዊውን መንግሥት በግልፅ ኃይል ተጠቅሞ ለመናድ እየሞከረ ነው" ነው ብለዋል።
ከቅብር ወራት ወዲህ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ውጥረት በተመለከተ ማዕከላዊው መንግሥት በይፋ መግለጫ ሲሰጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ላለፉት ጥቂት ወራት በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካካል የነበረው ውጥረት ከመካሰስ አልፎ በመሣሪያ በታገዘ ሁኔታ የአስተዳደር ተቋማትን መቆጣጠር ደረጃ ላይ ደርሷል።
በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ተሿሚዎች በመሻር የራሱን ኃላፊዎች መሾም ጀምሯል።
ከስድስት ወራት በፊት በደብረፂዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እና በአስተዳደሩ የተሾሙ ኃላፊዎች "እንደማይወክሉት" ገልጾ ነበር።
የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ባለፈው ዓመት መጨረሻ በተካሄደው 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ሥራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለዲፕሎማቶች በሰጡት መግለጫ አንደኛው የፓርቲው ክንፍ "በግልፅ አመፅ የሚቀሰቅስ ፕሮፖጋንዳ እየነዛ እንዲሁም አመፅ በመቅስቀስ ወደ ግጭት ለመግባት እየሞከረ ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት መተግበር የነበረባቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መመለስ እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም ማቋቋም በፓርቲው አባላት ምክንያት ተስተጓጉሏል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ "የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያዎችን አንቀበልም ብለዋል" በማለት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ችላ እንዳሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው የፕሪቶሪያው ስምምነት "ሁሉም አካላት በሀገሪቱ ሕግ እና መመሪያ እንዲተዳደሩ፤ ሕግ እንዲያከብሩ እንዲሁም በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙ ተቋማትን መመሪያ እንዲከተሉ" ያሳስባል።
ጌዲዮን በስብሰባ አዳራሹ ለተገኙ ዲፕሎማቶች ባስተላለፉት መልዕክት የውጭ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያወጧቸው መግለጫዎች "ሁለቱን አካላት" የሚወቅሱ ናቸው፤ ነገር ግን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ችላ እያለ እንዲሁም አመፅ እየቀሰቀሰ ያለው "አንደኛው አካል ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሩ የፌዴራሉ መንግሥት ሁኔታውን በጥንቃቄ እየተመለከተው መሆኑንም ተናግረዋል።
"ያለንን አቅም ተጠቅመን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የተኩስ አቁሙ እንዲቀጥል እና በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እናደርጋለን።"
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በትግራይ የተከሰተው ቀውስ ከተባባሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደሚወያዩ ተዘግቧል።
አቶ ጌታቸው ሐሙስ ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የሕዝብን ሠላም፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት፣ የአገሪቱን መረጋጋት እንደ መያዣ ከተጠቀመ አካል" ጋር እንዳይደራደሩ ጠይቀዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመሩት ቡድን እየወሰደ ያለው እርምጃን "እብደት" በማለት ድርጊቱ ክልሉን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።












