ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካንሰርን ቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል ስኬታማ ምርምር ተካሄደ
ከ50 በላይ የካንሰር ዓይነቶች ላይ የተሠራ ጥናት ካንሰርን በምርመራ ለማግኘት የሚወስደውን ጊዜ እንደሚያሳጥር ተገለጸ።
በሰሜን አሜሪካ በተካሄደው ጥናት የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የምርመራ ስልት ያልነበራቸው የካንሰር ዓይነቶች ይገኙበታል።
ምርምር ከተደረገባቸው የካንሰር ዓይነቶች ግማሹ በመጀመሪያ የስርጭት ደረጃ ላይ ሳሉ ሊደረስባቸው ተችሏል።
ካንሰር በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ሳለ በምርመራ ሲገኝ የተሻለ ሕክምና መስጠት ይቻላል።
'ዘ ጋላሪ ቴስት' የሚል ስያሜ የተሰጠው ምርምር የተደረገው በአሜሪካው መድኃኒት አምራች ግሬይል ነው።
የዘረ መል ናሙና በመውሰድ በደም ሕዋስ ውስጥ በመሰራጨት ላይ ያለ ካንሰር ላይ ለመድረስ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በጥናቱ 25,000 ሰዎች ከካናዳ እና አሜሪካ ተሳትፈዋል። ከ100 ሰዎች አንዳቸው ካንሰር እንዳለባቸው ታውቋል።
62% ያህሉ ካንሰር እንዳለባቸው የታወቀው ዘግይቶ ነው።
የግሬይል ፕሬዝዳንት ሰር ሀርፐል ኩማር "የተገኘው ውጤት አበረታች ነው" ብለዋል።
ከቢቢሲ ጋር ባደረጉተ ቆይታ፤ "አዳዲስ የካንሰር ዓይነቶችን ለማግኘት ምርምሩ ያግዛል። በጣም አደገኛ የሆኑ የካንሰር ዓይነቶችን ቀድመን ካወቅን የተሻለ ሕክምና መስጠት እንችላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በኦገን ኸልዝ ኤንድ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ የጨረራ ባለሙያ እና የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ኒማ ናባቪዝዳህ እንዳሉት፤ ግኝታቸው "የካንሰር ምርመራን ይለውጣል"።
"የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶችን ሳይዘገይ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ አግኝተናል። ስኬታማ ሕክምና ለመስጠት እና ሕመሙን ለመፈወስም ጉልህ ሚና አለው" ብለዋል።
በዩኬ የካንሰር ጥናት ማዕከል የሚሠሩት ናስር ተርቢ በበኩላቸው፤ "ጉዳት የማያደርሱ የካንሰር ዓይነቶችን በተጋነነ መጠን በምርመራ ማግኘት" አስጊ ይሆናል ብለዋል።
ካንሰር እንደሌለባቸው ከታወቁ ናሙናዎች መካከል 99 በመቶ ያህሉ በትክክልም ካንሰር እንደሌለባቸው በማረጋገጥ ረገድ ጥናቱ ውጤታማ ሆኗል።
ምርመራው ከጡት እና ከማሕጸን እንዲሁም ከሰገራ ምርመራ ጋር በመጣመር የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል።
ጥናቱ የተካሄደው በምርመራ ለማወቅ አስቸጋሪ በሆኑ የካንሰር ዓይነቶች ላይ ሲሆን፤ ይህም የእንቁላል እጢ፣ የጉበት፣ የሆድ፣ የሽንት ትቦ እና የጣፊያ ካንሰርን ይጨምራል።
ከ10 ናሙናዎች በዘጠኙ የካንሰሩ መነሻ ተደርሶበታል። የደም ምርመራ በማድረግ ካንሰርን ቀድሞ ማወቅ የሚቻልበትን መንገድም አመላክቷል።
የደም ምርመራ ማድረግ በካንሰር የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ስለመቀነሱ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ሳይንቲስቶች ገልጸዋል።
በለንደን የካንሰር ጥናት ማዕከል የሚሠሩት ፕ/ር ክሌር ተርንበል "ቀድሞ ካንሰርን ማግኘት በካንሰር የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ይቀንሳል? የሚለውን ለማወቅ ወጥ ያልሆኑ ናሙናዎች መወሰድ አለባቸው" ብለዋል።
የጥናቱ ውጤት 'ዩሮፕያን ሶሳይቲ ፎር ሜዲካል ኦንኮሎጂ' መጽሔት ላይ የሚታተም ይሆናል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንዳለው፤ ሦስት ዓመታት የወሰደና 140,000 ሰዎች የተሳተፉበት ጥናት በቀጣይ ዓመት ይፋ ይደረጋል።
ጥናቱ ስኬታማ ከሆነ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ላይ ሙከራ ይደረጋል።