በምሥራቅ ሐረርጌ በውርስ ምክንያት አባቱን በመግደል የተጠረጠረው በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, GW POLICE
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳ በውርስ ምክንያት አባቱን በመግደል የተጠረጠረው የ25 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ተጠርጣሪው ኢብራሂም ሐሰን አብደላ በጉራዋ ወረዳ ኤላ ጣጤሳ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩትን ወላጅ አባቱን ሐሰን አብደላ “አስቦ እና ተዘጋጅቶ” በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን የወረዳው ፖሊስ ገልጿል።
በዕድሜ መግፋት ምክንያት አባቱ የእርሻ መሬታቸውን በውርስ ለልጆቻቸው ያከፋፈሉበት ሁኔታ ያላስደሰተው ኢብራሂም ሐሰን በአባቱ ላይ ግድያ ፈጽሟል ተብሎ ነው በፖሊስ የተያዘው።
“አባቱን ለመግደል ተዘጋጅቶ፤ ሰው የሌለበትን አሳቻ ሰዓት ጠብቆ እና አባቱን ተከታትሎ ገድሏል” ተብሎ መጠርጠሩን የጉራዋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዋቅጋሪ ጀቤሳ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው ወንጀሉን የፈጸመው ባለቤቱን ጨምሮ ከሌሎች ጋር በመመካከር መሆኑን እና ተባባሪዎቹም የሟችን አስክሬን በመጣል፣ ተጠርጣሪን በመሸሸግ እና ማስረጃ ለማጥፋት በመሞከር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ አዛዡ ጭምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፖሊስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ ተጠርጣሪው አባቱን ከገደለ በኋላ አስክሬናቸውን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመተባበር ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጥሏል።
ዋና ኢንስፔክተሩ እንደሚሉት ከሆነ ሟች አድራሻቸው ሲጠፋ ተጠርጣሪው ከሌሎች ወንድም እና እህቶቹ ጋር ‘አባቴ ጠፍቷል’ በሚል ፍለጋ ሲያደርግ ነበር።
“በሦስተኛው ቀን ላይ ግን ለእህቱ የአባቱን አስክሬን አሳያት። እርሷ መጮኽ ስትጀምር እሱ በሩጫ ከአካባቢው ተሰወረ” በማለት የአባትየው ሞት ሲታወቅ እና የልጅ በግድያው ተጠርጣሪ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪው የአባቱን አስክሬን ለእህቱ አሳይቶ ካመለጠ በኋላ ፖሊስ ባደረገው አሰሳ በዚያው መንደር ውስጥ በተባባሪው ሰው ቤት ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።
የፖሊስ አዛዡ እንደሚሉት ከሆነ ከተጠርጣሪው ባለቤት እና ሸሽጎ ከደበቀው ግለሰብ በተጨማሪ የቀበሌው ሊቀ መንበርም የወንጀሉ ተባባሪ ናቸው በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስረዳሉ።
የሟች አስክሬን ከተጣለበት ከወጣ በኋላ አስክሬኑን ለምርመራ ለመላክ የተደረገውን ጥረት ሊቀ መንበሩ ማስቆማቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ ይገልጻሉ።
ሊቀ መንበሩ ከተጠርጣሪው ጋር የጥቅም ትስስር ስላላቸው የአካባቢውን ሰዎች አስገድደው የሟች አስክሬን እንዲቀበር ማስደረጋቸውን ይናገራሉ።
“ሊቀ መንበሩ ከተጠርጣሪው ገንዘብ ተቀብሎ ስለነበረ አስክሬኑ ‘ይቀበራል እንጂ የትም አይወሰድም። ሳር ለማጨድ ሲሞክር ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ሞተ እንጂ የገደለው የለም’ በሚል ምክንያት አስከሬኑ እንዲቀበር አደርጓል” ብለዋል ዋና ኢንስፔክተር ዋቅጋሪ ጀቤሳ።
እንደ ፖሊስ አባሉ ከሆነ አስክሬኑ ለምርመራ መላክ አለበት በማለት የተከራረኩትን ሊቀ መንበሩ እስከ ማሰር ደርሶ ነበር።
ይሁን እንጂ የወረዳው ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ጉዳዩን በመመርመር አስክሬን ከተቀበረበት ወጥቶ ለምርመራ ወደ ሐረር ከተማ መላኩን ገልጾ፣ ከተጠርጣሪው በተጨማሪ የተጠርጣሪውን ባለቤት እና ሊቀ መንበሩን ጨምሮ 5 ሰዎችን በወንጀል ተባባሪነት በመጠርጠር ማሰሩን ገልጸዋል።
ፖሊስ የአስክሬን ምርመራ ውጤት እየጠበቀ የተለያዩ ማስረጃዎችን በተጠርጣሪዎች ላይ እያሰባሰበ መሆኑን ገልጾ፤ ጉዳዩ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል ብሏል።












