‘ልጄ መናገር አልጀመረም፤ ምን ማድረግ ይሻለኛል?’

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወላጆች ልጆቻቸውን ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ማነጻጸራቸው የተለመደ ነው።
በተለይ የዕድሜ እኩዮቻቸው እያወሩ ሲጫወቱ ልጆቻቸው ዝም የሚሉ ከሆነ፣ ወይንም ለመናገር መቸገር ካስተዋሉ፣ ወይንም የሚናገሩትን ለመረዳት ሲቸገሩ ደንገጥ ማለታቸው አይቀርም።
ሁሉም ልጆች እኩል የእድገት ደረጃ የላቸውም። ቢሆንም ግን ወላጅ ሁሉ ልጆቻቸው ያለ አንዳች እክል ከእኩዮቻቸው ጋር ቢቀላቀሉ ደስታቸው ወደር የለውም።
አንዳንዴ ግን በተለምዶ ወንድ ከሆነ ለንግግር ይዘገያል በሚል ሲታለፍ ይስተዋላል።
በእርግጥ ልጅ መናገር ቻለ ማለት ያለ እክል ይጫወታል፣ ጓደኛ ያፈራል፣ ይግባባል፣ ዓለሙን ቀለል ያደርግለታል ማለት ነው።
ጥናቶች ከ10 ልጆች መካከል አንድ የንግግር ወይንም የቋንቋ መዘግየት ሊያጋጥመው ይችላል ይላሉ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም እና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን ዶክተር ፋሲል መንበረን አንድ ሕጻን በንግግር ዘገየ የሚባለው መቼ ነው? ስንል ጠይቀናቸዋል።
አንድ ልጅ በቋንቋ ወይንም በንግግር ዘገየ የሚባለው ለእርሱ እድሜ ከሚመጥነው በታች፣ የንግግር ወይንም የቋንቋ ሂደቱ ከሚጠበቀው በታች ሆኖ ሲገኝ፣ በማንኛውም ዕድሜ ላይ የንግግር ወይንም የቋንቋ መዘግየት አለ ይባላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ወላጆች መዘንጋት የሌለባቸው ሁሉም ሕጻናት አፋቸውን የሚፈቱበት የተለያየ ቅደም ተከተል አላቸው።
ሁሉም ልጅ የየራሱ ተፈጥሮ አለው። ሆኖም ግን አንዳንድ ሕጻናት በዕድሜያቸው ከሚጠበቀው ከስድስት ወር ወይንም ከአንድ ዓመት በላይ በሚዘገዩ ጊዜ በትክክል የቋንቋ ወይንም የንግግር መዘግየት አለባቸው ይባላል።
የንግግር ወይንም የቋንቋ መዘግየት ምንድን ነው?
ሕጻናት ሁለት ዓይነት የቋንቋ እድገት አላቸው ይላሉ ዶ/ር ፋሲል።
አንደኛው አንድን ነገር የመግለጽ፣ የማስረዳት ብቃታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ነገሮችን የመረዳት ብቃታቸው ነው።
አንድ ልጅ በእርሱ ዕድሜ የተነገረውን፣ የሚመጥነውን ነገር መረዳት ካቃተው ራሱ የንግግር ወይንም የቋንቋ መዘግየት ችግር አለበት ማለት ነው።
በተመሳሳይ ዕድሜው በሚመጥነው መልኩ ራሱን መግለጽ ካቃተው፣ ቃላት ካላወጣ፣ የንግግር መዘግየት ችግር አለበት ይባላል።
የሕጻናት በንግግር መዘግየት የመስማት፣ የመናገር እና የማስተዋል እክልን ሊያካትት እንደሚችል ዶ/ር ፋሲል ያብራራሉ።
የቋንቋ መዘግየት ተቀባይ፣ ገላጭ ወይም የሁለቱም ጥምረት ሊሆን ይችላል።
ተቀባይ የሆነ የቋንቋ ጉድለት የሚከሰተው ልጁ ቋንቋን የመረዳት ችግር ሲያጋጥመው ነው።
ገላጭ የቋንቋ ችግር የሚከሰተው ልጅዎ በቃላት የመግባቢያ ችግር ሲገጥመው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕጻናት ላይ የንግግር መዘግየትን የሚያስከትሉ ችግሮች
በዓለም ላይ በተጠናው ጥናት መሠረት የመጀመሪያው የንግግር የቋንቋ መዘግየትን የሚያመጣው ችግር የጆሮ አለመስማት ነው።
አጠቃላይ የመስማት ችግር ምክንያቱ ብዙ ነው። እነዚህም ተደጋጋሚ የጆሮ ኢንፌክሽን ወይንም ጉዳት ካለ፣ ከዚህ በፊት የማጅራት ገትር ተከስቶ ከሆነ የጆሮ የመስማት አቅሙ ሊቀንስ ይችላል።
ሕጻናት ደግሞ ንግግሮችን፣ ቃላቶችን ሰምተው ነው የሚለምዱት። ካልሰሙ ሊለምዱ አይችሉም።
በዚህም የተነሳ ላይናገሩ ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህም ቋንቋቸው ሊዘገይ ይችላል ማለት ነው።
አሁን አሁን እጅጉን እየበረከተ የመጣው ደግሞ ይላሉ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፋሲል፣ ከኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች ጋር ረዥም ጊዜ ማሳለፍ ነው።
ወላጆች ልጆች ዝም እንዲሉላቸው፣ አልያም ሥርዓት እንዲይዙ በሚል ቲቪ ከፍተው፣ ካልሆነ ስልክ ሰጥተው ሥራቸውን ማከናወን እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው።
ቲቪ እና ስልክ ንግግርን የሚያሳልጡ ነገሮች ባለመሆናቸው ትክክል አይደለም ይላሉ ዶ/ር ፋሲል።
“ኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች የአንድ ወገን ተግባቦት ብቻ በመሆናቸው ወደ ልጁ የሚደርስ እንጂ ከልጁ የሚመጣ የሁለትዮሽ ተግባቦት አይኖርም።”
አክለውም “ቴሌቪዥን ልጁ ቃላቶችን እንዲለምድ፣ እንዲያወራ አይጋብዘውም። ቃላቶችን ለማስለመድ ደግሞ በሁለት ወገን መስጠት እና መቀበል ያለበት የቃላት ልውውጥ ይፈልጋል። እንዲናገሩ ጊዜ መስጠት ይፈልጋል።”
ቲቪ እና ሞባይል ረዥም ጊዜ የሚያዩ ከሆነ መረጃው የሚመጣው ከአንድ ወገን ብቻ በመሆኑ በደንብ ላይረዱት ይችላሉ።
መረጃዎቹም በጣም ተከታታይ ይሆኑባቸው እና ቃላትን ላይዙ ይችላሉ።
የአሜሪካ የሕጻናት ሕክምና አካዳሚ ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ምንም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች ባያዩ ሲል ይመክራል።
ከሁለት ዓመት እስከ አራት ዓመት ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ ደግሞ፣ ከወላጆች ጋር በመሆን ቢበዛ 45 ደቂቃ ብቻ ማየት አለባቸው ሲል ያስቀምጣል።
እንደ ዶ/ር ፋሲል ማብራሪያ ሦስተኛው በሕጻናት ላይ የንግግር መዘግየት የሚያስከትለው የእድገት ውስንነቶች በዋናነት ኦቲዝም ነው።
ኦቲዝም ዋና ምልክቱ የቋንቋ የመግባባት ክህሎት ማነስ ሲሆን፣ ተጨማሪ ደግሞ ተደጋጋሚ የእግር እና የእጅ እንቅስቃሴዎች መኖር፣ መዝለል፣ አንድ ዓይነት ነገሮችን በተደጋጋሚ ማድረግ፣ በአንድ መጫወቻ ራስን መወሰን፣ በስም ሲጠሩ አለመመለስ፣ ከሌሎች ጋር ለመጫወት መቸገር፣ ትኩረት አለመስጠት የመሳሰሉት ምልክቶችም ይጠቀሳሉ።
ሆኖም ግን የቋንቋ ወይንም የንግግር መዘግየት ያለባቸው ሕጻናት በሙሉ ኦቲዝም አለባቸው ማለት አለመሆኑን ዶ/ር ፋሲል አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።
ይልቁኑስ ረዥም ጊዜ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚመጣን የንግግር መዘግየት ባለሙያዎች ቨርችዋል ኦቲዝም ይሉታል ሲሉ ያብራራሉ።
በሕጻናት ላይ የአእምሮ ሕመሞች እና የእድገት ውስንነቶች ከተከሰቱ፣ ለምሳሌ በወሊድ ወቅት መታፈን፣ ዳውን ሲንድሮም ካለ የቋንቋ መዘግየትን ያመጣሉ።
ልጆች የማኅበራዊ ግንኙነቶች በጣም ከቀነሱ ለምሳሌ ከእኩዮቻቸው ተነጥለው ለብቻቸው ካደጉ፣ ቤተሰብ ውስጥ ምንም ዓይነት ንግግር ከሌለ፣ የሚያዋራቸው ሰው ካጡ፣ ፀጥ ብለው የሚውሉ ከሆነ በዚህም የተነሳ ንግግራቸውም ሊዘገይ ይችላል።
ዶ/ር ፋሲል ለንግግር ወይንም የቋንቋ መዘግየት የመጨረሻ ምክንያት ብለው የጠቀሱት፣ የአፍ እና የላንቃ አፈጣጠር ችግሮች መኖርን ነው።
የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስቱ የልጁ ወንድ መሆን፣ ቤተሰብ ውስጥ ሌላ በንግግር የዘገየ ሰው ካለ፣ በቤት ውስጥ ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚነገር ከሆነ ለንግግር መዘግየት አጋላጭ ምክንያቶች ሊሆኑ አንደሚችሉም ጠቅሰዋል።
አክለውም “እነዚህ አጋላጭ ምክንያቶች እንጂ በራሳቸው ምክንያት አይደሉም” ይላሉ።
በሴቶች እና በወንዶች መካከል የሚታየው ልዩነት ከስድስት ወር በላይ ከሆነ ግን፣ ወንድ ነው ብቻ በማለት ቸል ማለት እንደማይገባም ይመክራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Dr. Fasil
ሕጻናት በየትኛው የዕድሜያቸው ክልል ምን ያዳብራሉ?
ሕጻናት ከተወለዱ ጀምሮ ድምጽ እየሰሙ ነው የሚያድጉት። ሕጻናት በማሕጸንም ሳሉ የእናታቸውን እና የአባታቸውን ድምጽ ይሰማሉ።
- ከተወለዱ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር አናባቢ የሚባሉት ድምጾች (አ፣ ኦ) በተደጋጋሚ ይላሉ። ከዚያ ደግሞ ድምጽ ወዳለበት ቦታ ዞር ማለት ይጀምራሉ።
- ከ4 ወር እሰከ ስምንት ወር ባለው ጊዜ ደግሞ ባ. . . ፓ የሚመስሉ ተነባቢ ድምጾችን በተደጋጋሚ ያወጣሉ። ወይንም ደግሞ ሰዎች ደምጽ ሲያወጡ ሰምተው እንዲደግሙ ይጠበቃል።
- ከ9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ደግሞ አባባ እና እማማን ይጀምራሉ።
- ልክ አንድ ዓመት ላይ ደግሞ አባባን ለአባታቸው፣ እማማን ለእናታቸው ብቻ መስጠት መቻል አለባቸው።
- ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ባለው ከአራት እስከ ሰባት ቃላት በደንብ ያውቃሉ። በተጨማሪም ምልክቶችን መረዳት ይችላሉ። ይህም ማለት በእጅ እና በፊት የሚያዩትን ቀላል ምልክቶች እንደ አይሆንም ዓይነት ምልክቶችን መረዳት መቻል አለባቸው።
- ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ደግሞ ከ10 እስከ 20 ቃላቶችን ያውቃሉ። ከዚያ በተጨማሪም ተንተባትበው የሚናገሩት ነገር ሃምሳ በመቶ ያህል ለሰው የሚረዳ መሆን አለበት።
- ከሁለት ዓመት እስከ ሦስት ዓመት ደግሞ እስከ 200 ቃላቶችን መልመድ አለባቸው።
- የአራት ዓመት ልጅ ዓረፍተ ነገር መስርቶ የሚፈልገውን ነገር መናገር መቻል አለበት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወላጆች ምን ማድረግ አለባቸው
ሕጻናት ፍቅር ብቻ ሳይሆን የተቀላጠፈ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ማነሳሳት ይፈልጋሉ። ገና ከመወለዳቸው ጀምሮ ማናገር እና ማጫወት መቻል አለብን።
በእያንዳንዱ ዕድሜ የሚጠበቀውን ደግሞ ወላጆች በማንበብ ልጆቻቸው በእድሜያቸውን የሚጠበቀውን ነገር እያደረጉት ነወይ? የሚለውን መከታተል እንደሚያስፈልግ የሕክምና ባለሙያው ገልጸዋል።
ልጆች በየእድሜ ክልላቸው የሚጠበቀውን ለውጥ ማሳየት ካልቻሉ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በመጠበቅ ወደ ሕክምና ባለሙያ (ሕጻናት ሐኪም) ዘንድ መውሰድ የመጀመሪያው የወላጆች እርምጃ መሆን እንዳለበት ዶ/ር ፋሲል ያስቀምጣሉ።
አብዛኞቹ ለንግግር መዘግየት ምክንያት የሆኑ ነገሮች የሚታከሙ እና የሚቀየሩ ናቸው ሲሉ ያክላሉ።
የአፍ ውስጥ አፈጣጠር፣ የትናጋ ችግር ወይንም ደግሞ፣ ረዥም ሰዓት ቲቪ ላይ የሚውል ልጅ ከሆነ በሕክምና እና በንግግር ቴራፒ መስተካከል ይቻላል።
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የንግግር መዘግየት የገጠማቸው ሕጻናት በንግግር ቴራፒ ባለሙያ ከታገዙ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር ባለው ውስጥ ለውጥ ማሳየት እንደሚጀምሩ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስቱ ገልጸዋል።
“ኦቲዝም ከሆነ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።”
ረዥም ጊዜ ቴሌቪዥን እና ሞባይል ላይ የሚያሳልፉ ልጆች የሚያሳዩት ምልክት ከኦቲዝም ጋር በጣም እንደሚመሳሰል የሚናገሩት ባለሙያው፤ ንግግራቸው ዝም ያለ፣ በጣም ኃይለኛ፣ ስሜታቸውን መግለጽ የሚችሉት በመጮህ እና በማልቀስ ብቻ ይሆናል ይላሉ።
አክለውም ልክ እንደ ኦቲስቲክ ሕጻናት ስማቸው ሲጠራ ምላሽ እንደማይሰጡ ያስረዳሉ።
ስለዚህ ቲቪ እና ሞባይል ከሁለት ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት አለመፍቀድ፣ ከተፈቀደም ለአጭር ሰዓት ከወላጅ ጋር አብሮ ብቻ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።












