ሚኒስትሩ በአረብ አገራት የአልኮል መጠጥ የሚያዘጋጁ ኬንያውያንን ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኬንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአረብ አገራት የሚገኙ ዜጎቻቸው የአልኮል መጠጥ በማዘጋጀት እና በመሸጥ ለችግር እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናገሩ።
ሚኒስትሩ አልፍሬድ ሙቱዋ እንደተናገሩት ኬንያውን የአልኮል መጠጦች ሕገወጥ በሆኑበቻው አገራት ‘ቻንጋ’ የተባለውን ቤት ውስጥ የሚዘጋጅ መጠጥ ከመጥመቅ እና ከመሸጥ ጋር ስማቸው መነሳቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
“በሙስሊም አገራት ውስጥ ከሁሉ ሕገወጥ ድርጊቶች ሁሉ የከፋ በሆነው፣ ኬንያውያን ቻንጋ በመዘጋጀት ለሌሎች አፍሪካውያን በማቅረብ ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው ልቤን ሰብሮታል. . .” በማለት ሚኒስትሩ ሲቲዝን ለተባለው ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።
ጨምረውም የአገራቸው ዜጎች እንዲህ ባለው ሕገወጥ ተግባር ላይ መሳተፋቸው፣ የኬንያ መንግሥት በውጭ ያሉ ዜጎቹ ደኅንነት እንዲጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ በዜጎቻቸው ላይ የሚፈጸመውን ሕገወጥ ድርጊት በተመለከተ የተናገሩት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ጥቃትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች የሚገጥማቸውን ኬንያውያን በተመለከተ በተጠየቁበት ወቅት ነው።
የኬንያ መንግሥት በአረብ አገራት ውስጥ ያሉ ዜጎቹ ደኅንነት እንዲሻሻል ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን አልፍሬድ ሙትዋ ተናግረዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይነት የተሾሙት ሚኒስትሩ ወዲያውኑ የመጀመሪያ ጉዟቸውን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያደረጉ ሲሆን፣ የዜጎቻቸው ሁኔታ “እንደተባለው የከፋ እንዳልሆነ” ተናግረዋል።
“ዋናው ችግር አንዳንድ ኬንያውያን ወደዚያ ሲሄዱ በሕገወጥ እና በወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፈው መገኘታቸው ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ሙቱዋ ገናግረዋል።
በርካታ አፍሪካውያን ለሥራ በሚሄዱባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ሙስሊም አገራት ውስጥ የአልኮል መጠጥ ማዘጋጀት፣ መሸጥ እና መጠጣት የተከለከለ ድርጊት ነው።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኬንያውያን በመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት ውስጥ ከቤት ውስጥ ሥራ ጀምሮ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
በዚህ ጊዜም ጥቂት የማይባሉ ኬንያውያን በደሎች እንደሚገጥማቸው የሚዘገብ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግሥትም የዜጎቹን መብትና ደኅንነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።












