እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሟን የዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች አስታወቁ

እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች መሆኑን የዓለም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተመራማሪ ምሁራን አስታወቁ።

የዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራን ማኅበር (IAGS) ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ድርጊት በተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ስምምነት ላይ የተቀመጠውን የሕግ ፍቺ ያሟላ ነው ብሏል።

ማኅበሩ ባቀረበው ባለ ሦስት ገጽ የውሳኔ ሃሳብ ላይ የእስራኤል ጦር በጋዛ ላለፉት 22 ወራት ባካሄደው ጦርነት፣ ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር የሚስተካከል፣ የጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ሲል ዘርዝሮታል።

የዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ምሁራን ማህበር (IAGS) በዓለም ላይ ከሚገኙ በዘርፉ ላይ ጥናት እና ምረምር ከሚያደርጉ ማኅበራት መካከል ቀዳሚው ሲሆን በርካታ የሆሎኮስት ባለሙያዎችን ያካትታል።

ከ 500 አባላቱ መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 86 በመቶ የውሳኔ ሃሳቡን ደግፈዋል።

በእስራኤል ፖሊሲዎች እና ድርጊቶች ላይ ጠቅለል ያለ ግምገማውን ያቀረበው የመግለጫው ክፍል በጤና አጠባበቅ፣ በእርዳታ እና በትምህርት ዘርፎች ላይ ጨምሮ ለኅልውና በሚያስፈልጉ ሠራተኞች እና መገልገያዎች ላይ በሰፊው ጥቃት መፈጸሙን አትቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅት ዩኒሴፍ እንዳተገለፀው ፍልስጤማውያን በጋዛ ዘራቸው እንዲቀጥል ወሳኝ የሆኑ 50,000 ሕጻናት መገደላቸውን ማኅበሩ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የውሳኔ ሃሳቡ የእስራኤል መሪዎች በግዛቱ ውስጥ በአጠቃላይ መኖሪያ ቤቶችን ከማፍረስ ጎን ለጎን ፍልስጤማውያንን በሙሉ ከጋዛ በግዳጅ ለማባረር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጉልቶ ያሳያል።

አይኤጂኤስ የእስራኤል መሪዎች በጋዛ ፍልስጤማውያንን ከሰብአዊነት በማዋረድ የሰጡትን መግለጫዎች የተመለከተ ሲሆን፣ ሁሉንም እንደ ጠላት በመፈረጅ "ጋዛን ለማፈራረስ" እና ወደ "ሲኦል" ለመቀየር ቃል ገብተው መንቀሳቀሳቸውን ተመልክቷል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱ "በሐማስ ውሸት" ላይ የተመሰረተ እና እና ደካማ ጥናትን መሰረት ያደረገ ነው ሲል የገለጸው ሲሆን "ለሕግ ባለሙያዎቹ አሳፋሪ ነው" ብሏል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመባት ራሷ እስራኤል ነች ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ የምትወስደው እርምጃ የዘር ማጥፋት አለመሆኑን በመግለጽ ራሷን እየተከላከለች መሆኑን ትገልጻለች።

የአይኤጂኤስ ምሁራን ሐማስ በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎች መግደሉ እና 251 ማገቱ ወንጀል ቢሆንም የእስራኤል ምላሽ በሐማስ ላይ ብቻ ሳይሆን መላውን የጋዛ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው ይላሉ።

እአአ የ1948ቱ የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ኮንቬንሽን በናዚ ጀርመን አይሁዶች ላይ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ተከትሎ የፀደቀ ሲሆን የዘር ማጥፋት ወንጀልን "አንድን ብሄር፣ ጎሳ፣ ዘር ወይም የሀይማኖት ቡድን በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የሚፈጸም ወንጀል" ሲል በይኖታል።

ከዚህ ቀደም ሁለት የእስራኤል ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ነው ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በርካታ የምዕራባውያን አገራት የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ነው የሚልን የፍርድ ቤት ብይን ብቻ እንደ ገዢ እንቆጥራለን ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት በበኩሉ የእስራኤል ጦር በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ነው በሚል በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ እየመረመረ ይገኛል።

እስራኤል በበኩሏ ክሱን አጥብቃ በመቃወም "ፍጹም መሠረተ ቢስ" እና ሐሰተኛ ስትል ውድቅ አድርጋዋለች።

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያልሰጠ ሲሆን እስራኤል መከላከያዋን እስከ ጥር 2026 ድረስ እንድታቀርብ ፈቅዷል።

እስራኤል ክሱን ፀረ ሴማዊ ነው ያለች ሲሆን አይሁዶች "ለደም ካሳ" ሲሉ የክርስትያን ልጆችን ይገድላሉ የሚለውን ሐሰተኛ እና የኖረ ውንጀላ በመጥቀስ አስተባብላለች።

አይኤጂኤስ የውሳኔ ሃሳባቸው ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከሚቀርብ ከማንኛውም ክስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ተናግሯል።

ሰኞ ዕለት በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ እስካሁን 63,557 ሰዎች መገደላቸውን እና 160,660 መቁሰላቸውን ተናግሯል።