የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ የተሰደዱ ነጭ ዜጎቻቸውን ፈሪዎች አሉ

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ልጆቻቸውን ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ ወደ አሜሪካ በስደት የተጓዙ 59 ነጭ የአገሬው ዜጎችን "ፈሪዎች" በማለት "በቅርቡ ይመለሳሉ" ሲሉ አጣጣሉ።

አፍሪካነርስ የሚባሉት ነጭ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ መድልኦ ደርሶባቸዋል በሚል የጥገኝነት ፈቃድ ከሰጧቸው በኋላ ሰኞ ዕለት አሜሪካ ደርሰዋል።

ይሁን እንጂ ራማፎሳ ለመውጣት የፈለጉት ዜጎች በአፓርታይድ ዘመን የተፈፀመውን ኢ-እኩልነት ለማስተካከል በሚወሰዱ እርምጃዎች ደስተኛ ያልሆኑ ናቸው ብለዋል።

"ደቡብ አፍሪካዊያን ጠንካሮች ነን። ችግሮቻችንን ጥለን አንፈረጥጥም። እዚህ መቆየት እና ችግሮቻችንን መፍታት አለብን። ጥለህ የምትፈረጥጥ ከሆነ ፈሪ ነህ፤ እና ይህ የፈሪዎች እርምጃ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ትራምፕ እና የቅርብ አጋራቸው ነጭ የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆነው ኢለን መስክ በደቡብ አፍሪካ ነጭ አርሶ አደሮች ላይ "የዘር ማጥፋት" ተፈፅሟል የሚሉ ሲሆን፤ ይህም በሰፊው ውድቅ የተደረገ ነው።

አሜሪካ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከነጭ አርሶ አደሮች መሬት ያለ ካሳ ወስዷል የሚል ክስም ታቀርባለች።

በአናሳ ነጭ ደቡብ አፍሪካውን ለአስርት ዓመታት የነበረው አገዛዝ ካበቃ ከ30 ዓመታት በኋላም ጥቁር አርሶ አደሮች ከአገሪቱ የእርሻ መሬት ውስጥ የከፊሉ ብቻ ባለቤት ናቸው።

አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬት አሁንም በነጮች እጅ ውስጥ መሆኑ ቁጣን አስከትሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ጥር ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ለሕዝብ ጥቅም እና እኩልነት ሲባል መንግሥት የግል መሬትን ያለ ካሳ የሚወርስበት አወዛጋቢ ሕግ አፅድቀዋል።

በዚህ ሕግ መሰረት እስካሁን የተወረሰ መሬት እንደሌለ ግን መንግሥታቸው አስታውቋል።

ትራምፕ በአብዛኛው ከደች መጥተው የሰፈሩ ነጮች ተወላጅ የሆኑ ደቡብ አፍሪካዊያን "መጥፎ ሁኔታን" እየሸሹ ነው በሚል አሜሪካ እንዲሰፍሩ ፈቅደዋል።

ራሞፎሳ በበኩላቸው እነዚህ ዜጎች ወደ አሜሪካ የሚጓዙት የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት "ተመራጭ" ባለመሆናቸው ነው ብለዋል።

"ነጩንም ጥቁሩንም ካያችሁ አገር ውስጥ የቆዩት አገራቸው ስለሆነ ነው። እና ችግሮቻችንን ጥለን መሮጥ የለብንም። እዚህ መቆየት እና ችግሮቻችንን መፍታት አለብን" በማለትም አክለዋል።

የፕሬዝዳንቱ "ፈሪ" የሚለው አስተያየት በማኅበራዊ የትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ እንደ ስድብ በመታየት ብዙዎችን አስቆጥቷል።

ወደ አሜሪካ ያቀኑት ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን በአሜሪካ ባለስልጣናት አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን "በአመፅ እና በሽብር" ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ራማፎሳ ይህን በማጣጣል "በአህጉሪቱ ቅን ገዥዎች ለመቆየት መጥተው ያላባረርናቸው ብቸኛ አገር እኛ ነን" ብለዋል።

ሰኞ ዕለት አሜሪካ የደረሱ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን የስደተኛን መስፈርት አያሟሉም ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

የደቡብ አፍሪካ የመሬት ሕግ በዘረኛ መድልዎ የተሞላና የአፓርታይድ ጊዜ ቅሪት በመሆኑ ትችት የሚሰነዘርበት ሲሆን ላለፉት ሦስት አሥርታት ባለመሻሻሉም ተነቅፏል።

ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን 90 ሕዝብ ሆነው 4 በመቶ ብቻ መሬት እንዳላቸው እአአ በ2017 የወጣ ሪፖርት ይጠቁማል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያደገው የትራምፕ አማካሪ ኢሎን መስክ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነጭ አርሶ አደሮች ላይ "የዘር ጭፍጨፋ" ፈጽሟል ሲል በተደጋጋሚ ይሰማል።

ነጭ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ ገብተው የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ዶናልድ ትራምፕ "ቅድሚያ" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑ መገለጹን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አሜሪካ "በፖለቲካ ምክንያት" የምትፈጽመው ይህ ድርጊት የደቡብ አፍሪካን "ሕገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓትን" የናቀ ነው ብሏል።

በደቡብ አፍሪካና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል።