ግጭት ውስጥ የከረመው የጋምቤላ ክልል መንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Gambella town communication
በጋምቤላ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሥራ አቋርጠው የነበሩት የክልሉ መሥሪያ ቤቶች፤ "ሁሉም" ሠራተኞቻቸው ወደ ሥራ ስለመመለሳቸው "ጥብቅ ቁጥጥር" እንዲደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጣቸው። የፀጥታ ችግር ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ሠራተኞች "ያለ ስጋት ገብተው እንዲወጡ ጥበቃ" እንደሚደረግላቸውም ተገልጿል።
የጋምቤላ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው ረቡዕ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም. በክልሉ ለሚገኙት 53 መሥሪያ ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ ነው። ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ የተቀሰቀሰው የጋምቤላ ክልል ግጭት ከታኅሣሥ ወር ሁለተኛ ሳምንት አንስቶ ተባብሶ ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት ለሦስት ሳምንት ያህል ለሚሆን ጊዜ የክልሉ መሥሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ሥራ አቁመው መሰንበታቸውን አንድ የክልሉ መንግሥት ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ግን መሥሪያ ቤቶች በተወሰነ ደረጃ እየተከፈቱ መሆኑን የሚናገሩት ምንጩ፤ የክልሉ መንግሥትም ወደ ሥራ የተመለሱት የትኛዎቹ ቢሮዎች እንደሆኑ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን አስረድተዋል።
ፐብሊክ የሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የጻፈውም ደብዳቤ፤ "በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ላለፉት ሦስት ሳምንታት" የመሥሪያ ቤቶቹ አገልግሎት "መስተጓጎሉን" ጠቅሷል።
በአሁኑ ሰዓት ግን "በጋምቤላ ከተማ ብሎም የፀጥታ መደፍረስ ችግር ባጋጠማቸው ቦታዎች አንጻራዊ ሠላም እየሰፈነ" እንደሆነ ገልጿል።
በዚህም የተነሳ የክልሉ መንግሥት፤ መሥሪያ ቤቶች "ወደ መደበኛው አገልግሎት እንዲመለሱ እና ሁሉም የቢሮ ሠራተኞች በመደበኛ ሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ" መወሰኑን ደብዳቤው ያስረዳል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ እንደሚያስረዱት፤ ይህ ውሳኔ የተላለፈው፤ የጋምቤላ ክልል ካቢኔ እና የፀጥታ አካላት ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ "በዝግ" እያደረጉት ባለው ስብሰባ ላይ ነው።
የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች "ለጉዳዩ አጽንኦት" ሰጥተው "የተቋረጠውን መደበኛ የመንግሥት ሥራ" ከታኅሣሥ 22 ጀምሮ እንዲያስጀምሩ ደብዳቤው አሳስቧል። "ሁሉም ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ስንል እናሳስባለን" ብሏል።
የክልሉ መንግሥት ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቢያዝዝም አሁንም ድረስ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ምንጩ ጠቅሰዋል።
ይህንኑ ጉዳይ ያመለከተው የክልሉ ፐብሊክ የሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ደብዳቤም፤ በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ ቢሮዎች "ጥበቃ" እንደሚደረግ አስታውቋል።
ቢሮው፤ "የፀጥታ ችግር ተጋላጭ በሆነ ቦታ የሚገኙ ቢሮዎች ሠራተኞቻቸው ያለ ስጋት ገብተው እንዲወጡ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው የክልሉ መንግሥት ያሳስባል" ሲል በደብዳቤው አስፍሯል።
እነዚህን አካባቢዎች የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የሚገልጹት ምንጩ፤ ስጋት ያለባቸውም ቢሮዎች ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል እንዲመደብላቸው ይጠይቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለዋል።















