በጋምቤላ ክልል የፀጥታ ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች ላልተወሰነ ጊዜ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Gambella Press Secretariat
በጋምቤላ ክልል ለሳምንታት ከዘለቀው አለመረጋጋተት ጋር በተያያዘ የፀጥታ ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ።
የክልሉ መንግሥት ረቡዕ ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የክልሉ ዋና ከተማን ጨምሮ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ ከልክሏል።
የሰዓት እላፊው ተግባራዊ የሚሆነው ከረቡዕ ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም. ሲሆን እስከ መቼ ድረስ እንደሚቆይ ግን አልተገለጸም።
በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር በሚል ከኅዳር 30/2018 ዓ.ም. አንስቶ ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ እና ሰው ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከልክል የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ ነበር።
የክልሉ መንግሥት በተጨማሪም ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውም ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አስታውቋል።
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበር እና በማስከበር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት መግለጫው ጠይቋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚፈጸሙ ጥቃቶች የተነሳ አለመረጋጋት ተፈጥሯል።
በክልሉ ከኅዳር 28/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ (አቦል)፣ በጋምቤላ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡመድ ኡጁሉ ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል።
በክልሉ ዋና ከተማ እና በአካባቢው ባሉት ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተፈጠረው ግጭት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ንብረት መውደሙን ተከትሎ ባንኮችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቋርጠው ነበር።
ሰኞ ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም. የመከላከያ እና የፌደራል የፀጥታ አካላት መሰማራታቸውን ተከትሎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለቢቢሲ ገልጿል።
የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአካባቢው በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ በክልሉ ለሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የምግብ ሥርጭት እና የውሃ አቅርቦት ለጊዜው ተቋርጧል ብሏል።
በጋምቤላ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ዙሪያ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚነዛው "ሐሰተኛ መረጃ" በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተሠጠው ይበልጥ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል ሲል ዩኤንኤችሲአር ባወጣው መግለጫ ላይ አስጠነቅቋል።
በክልሉ የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ በስደተኞች እና በስደተኛ ተቀባዩ ማኅበረሰብ ላይ "የጥላቻ ንግግር" የሚነዙ ሁሉም ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ የስደተኞችን፣ የተቀባይ ማኅበረሰቦችን እና የረድኤት ሠራተኞችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሠራ መኾኑን ገልጾ፣ በትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፍ የተገኘ ስደተኛ ግን በአገሪቱ ሕግ ይዳኛል ሲል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል ያሏቸውን አካላት በቁጥጥር ሥር እያዋሉ መሆኑን የገለፀው የክልሉ መንግሥት እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ጅር አንደሚገኙ ያለው ነገር የለም።
ኢሰመኮ ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት ተገቢ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ብሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጋምቤላ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶችና የሰላም መደፍረሶች በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችንና እርምጃዎችን እየተፈታተኑ እንደሆነ መናገራቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።














