ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንጎላ ትልቅ የሕክምና ማዕከል የከፈተው ኢትዮጵያዊ ዶክተር
በልጅነቱ አስተማሪዎቹም ሆኑ የቅርብ ቤተሰቦቹ ‘ስታድግ ምን እንድትሆን ነው የምትፈልገው?’ ብለው ሲጠይቁት ‘ሐኪም ወይም ደግሞ መሃንዲስ መሆን ነው የምፈልገው’ ይል እንደነበር ያስታውሳል።
ይሁን እንጂ ከሌላው በተለየ የሕክምናው ዘርፍ ላይ እንዲያተኩር ምክያት የሆነውን አጋጣሚን አይረሳውም።
በልጅነቱ ከወላጅ እናቱ በላይ ከአያቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበረው የሚናገረው ዶ/ር ዳዊት አማረ፣ ከዕለታት አንድ ቀን አያቱን የስትሮክ አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል አቀኑ።
የአያቱን እግር ተከትሎ ወደ ሕክምና ተቋም ያመራው የያኔው ብላቴና ዳዊት፣ አስፈላጊውን ሕክምና አግኝተው ተሽሏቸው ለቤታቸው ይበቃሉ ብሎ ተስፋ ቢያደርግም፣ እዚያው ሆስፒታል አያቱን ያጣበት ሁኔታን መቼም አይረሳውም።
ተረኛ የሕክምና ባለሙያዎች አስቸኳይ እርዳታ ባለማድረጋቸው የተነሳ አያቱ አካላቸው መንቀሳቀስ ሳይችል እንደቀረ እና በኋላም ሕይወታቸው እንዳለፈ የሚናገረው ዶ/ር ዳዊት “ይሄኔ ሐኪም ብሆን ኖሮ የአያቴን ሕይወት እታደግ ነበር” የሚል ቁጭት እንዳሳደረበት ያስታውሳል።
ዶ/ር ዳዊት የአያቱን ሕይወት ለመታደግ ባይታደልም የብዙ ሺዎችን ሕይወት መታደግ ግን ችሏል።
“ሐኪም ሲኮን የበሽተኞችን ችግር እየሰሙ መኖር ነው” የሚለው ዶ/ር ዳዊት፣ ቢሆንም ታካሚዎች ድነው ወደ ቤታቸው በጤና ሲመለሱ አይቶ የሚገኘው የህሊና እርካታ ወደር የለሽ እንደሆነ ይናገራል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ ሐኪም መሆን እንደሚፈልግ የተገነዘቡት የቅርብ ሰዎች “ሕክምና ለማጥናት ረጅም ጊዜ ይፈጅብሃል” የሚል ተስፋ አስቆራጭ ሀሳብ ይሰጡት እንደነበር የሚናገረው ዶ/ሩ፣ እሱ ግን የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የመሆን ህልሙን እውን ማድረግ ችሏል።
“አያቴን የስትሮክ ችግር ገጥሟት በዚያ ላይ ደግሞ ደም ግፊት ስለነበራት በቂ ሕክምና ካለማግኘትዋ የተነሳ አካላዋ ፓራላይዝድ ሆኖ የማትንቀሳቀስ እና የማታወራ ሆና ስመለከት በድንጋጤ ተጨናንቄ ነበር። ከዚህ በኋላ ነበር 7 ዓመትም ሆነ 10 ዓመት፣ ሕክምና አጥንቼ ዶ/ር መሆን እንዳለብኝ ለራሴ ቃል የገባሁት” ይላል።
አክሱም ከተማ የተወለደው ዶ/ር ዳዊት አማረ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው አክሱም ካጠናቀቀ በኋላ በ1991 ዓ.ም. የሕክምና ትምህርቱን ያጠናው በጅማ ዩኒቨርስቲ ነው።
በዩኒቨርስቲው 6 ዓመታት የሕክምና ትምህርቱን ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ በዓዲግራት ሆስፒታል ከተራ ሐኪምነት እስከ ሜዲካል ዳይሬክተርነት ደረጃ ሠርቷል።
ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ገብቶ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ካጠና በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው አዲስ ሕይወት ሆስፒታል ተቀጥሮ መሥራት እንደጀመረ የሚናገረው ዶ/ር ዳዊት፣ በቆይታው ከኢትዮጵያ ውጭ ሄዶ ተጨማሪ ልምዶችን አግኝቷል።
ብዙም ሳይቆይ በአዲስ አበባ ከተማ የራሱን ክሊኒክ ከፍቶ መሥራት ጀመረ።
“በአውሮፓ እና እስያ አገራት ተመላልሼ ባገኘሁት የሕክምና ልምድ በአገሬ ለመሥራት ፍላጎቱ ነበረኝ” የሚለው ዶ/ር ዳዊት አንጎላ ከሚኖር ወዳጁ የሰማው ግን ውሳኔውን አስቀየረው።
አንድ ወዳጁ አንጎላ ሀብታም አገር ብትሆንም የሕክምና አገልግሎቱ ግን እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይነግረዋል።
ዶ/ር ዳዊት በአዲስ አበባ ከተማ 22 ተብሎ በሚጠራው ሰፈር 25 ዶክተሮቹን ቀጥሮ የሚያሠራው ሜዲስታር የሕክምና ማዕከል ባለቤት ነው።
ከጓደኛው ስለአንጎላ የሰማው ነገር እና እዚያም በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን እንደሚኖሩ መገንዘቡ ሥራውን ወደ ውጭ አገር ለማስፋት እንዲያስብ አደረገው።
“በአንጎላ ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነሱም የጤና ችግር ሲገጥማቸው በራሳቸው ቋንቋ አስረድተው አገልግሎት ማግኘት አለባቸው ብለን እናምናለን። በተለይም አንድ ታካሚ በሽታውን ለማስረዳት በቋንቋ ችግር ምክንያት ተጨማሪ በሽታ ይዞ መመለስ የለበትም።”
ዶ/ር ዳዊት ከሁለት ኢትዮጵያውያን የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ይህን ችግር ይፈታል ብለው ያሰቡትን እና አንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገንበታል ያሉትን 'ግሬስ ሜዲካል ሴንተር' የተባለ የሕክማና ማዕከል በአንጎላ መዲና ገንብተው ለሥራ አብቅተዋል።
ግሬስ ሜዲካል ሴንተር ያረፈበትን ህንጻ ለመገንባት ከሁለት ዓመት በላይ እንደፈጀ እና ቀዶ ሕክምና፣ የአዋቂዎች እና ልጆች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 60 ሠራተኞች ያሉት መሆኑን ከመሥራቾቹ አንዱ የሆነው ዶ/ር ዳዊት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ግሬስ ሜዲካል ሴንተር በአንጎላ መንግሥት የሁለተኛ ደረጃ ፍቃድ እንደተሰጠው እና ታካሚዎች ተኝተው የሚታከሙባቸው 40 ክፍሎች የያዘ የሕክምና ማዕከል ነው።
በሚቀጥለው ምዕራፍ ደግሞ 150 መኝታ እንዲሁም 150 የሕክምና ባለሙያዎች በመቅጠር በአንጎላ ከቀዳሚዎቹ የሕክምና ማዕከላት መካከል አንዱ የማድረግ ራዕይ እንዳላቸውም ዶ/ር ዳዊት ለቢቢሲ ገልጿል።
በኢትዮጵያ የዳበረ ልምድ ያላቸው ሐኪሞች በመንግሥት ከሚተዳደሩ ሆስፒታሎች ወጥተው ወደ ግሉ የሕክምና ማዕከላት መሄድ የተለመደ ነው።
በዚህ ምክንያት ሀብታም የተሻለ ህክምና የሚያገኝበት በዚያው ልክ ደግሞ ድሃው በቂ ሕክምና የማያገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱ ይነገራል።
ብዙ ሰዎች መርዳት እየቻለ በቂ ደሞዝ ስለማይገኝበት የራሱን ክሊኒክ ከፍቶ እንዲሠራ መገደዱን የሚናገረው ዶ/ር ዳዊት አማረ “ለምሳሌ እኔን ብትጠይቁኝ መርዳት ከምችለው ሕዝብ ሁለት ፐርሰንት ብቻ ነው የማገለግለው። በዚህ ደግሞ ደስተኛ አይደለሁም” ይላል።
“ቢሆንም መንግሥት የሚከፍለው ደሞዝ አይደለም ሊያረካ ለመኖርም ፈታኝ ስለሚሆን ጥግን ይዞ ሕይወትን ለመምራት ነው የሚገፋው” የሚለው ዶ/ር ዳዊት በአንጎላ የከፈተው የሕክምና ተቋም ባለሙያዎቹን ከኢትዮጵያ እንደማያሸሽ ያስረዳል።
በመጀመሪያው ዙር ከተቀጠሩት ባለሙያዎች በስተቀር አንጎላ እና ኢትዮጵያ እየተመላለሱ የሚሠሩ ስፔሻሊስቶችን በመቅጠር ችግሩን ለማቅለል ጥረት እንደሚያደርግም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ተናግሯል።
በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተንቀሳቅሶ የሐኪሞቹን ሕይወት ለማየት ዕድል ገጥሞት እንደነበር የሚናገረው ዶ/ር ዳዊት፣ የሕክምና ዶክተሮች ከሙያቸው በተጨማሪ የግብርና ሥራም እንደሚሠሩ መመልከቱን ያናገራል።
“በኢትዮጵያ ግን ሌላው ቀርቶ መኖሪያ ቤት እና ሮጥ ብሎ ታካሚዎችን የሚያገለግለበት መኪና ለማግኘት የሚቸገር ሐኪም ነው ያለው። በሕክምናው መነጽር አንድ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ተመላልሶ የሚያገልግልባት መኪና ማግኘት መሠረታዊ ፍላጎት ነው” ይላል።
ለዚም እንደ ዶ/ር ዳዊት ገለጻ መንግሥት ለሐኪሞች መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ በማመቻቸት እንዲሁም መኪና ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ በማድረግ የሕክምናው ዘርፍ ማሻሻል እንደሚችል ይጠቁማል።