ሶርያ አይኤስን ለመዋጋት የተመሠረተውን አሜሪካ መር ጥምረት ልትቀላቀል ነው

ሶርያ፤ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድንን ለመወጋት የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ጥምረት እንደምትቀላቀል አንድ የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን አረጋገጡ። ይህ ስምምነት በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ተነግሯል።

ውሳኔው ይፋ የተደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶርያው ፕሬዝዳንት አሕመድ አልሻራ ጋር በዋይት ሀውስ በተገናኙበት ወቅት ነው። በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የሶርያ መሪ ጉብኝት ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የሶርያው ፕሬዝዳንት ከፎክስ ኒውስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ፤ ጉብኝቱ ሶርያ ከአሜሪካ ጋር በትብብር የምትሠራበት "አዲስ ዘመን" አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሜሪካ መንግሥት የሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ለነበሩት አዲሱ የሶርያ ፕሬዝዳንት አልሻራ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

በውሳኔው መሠረት ሶርያ አይኤስን ለማጥፋት የተቋቋመውን ዓለም አቀፍ ጥምረት የምትቀላቀል 90ኛዋ አገር ትሆናለች። ጥምረቱ፤ ኢስላሚክ ስቴት ተብሎ የሚጠራው ቡድን የቀሩ አባላትን ለማጥፋት እና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገውን የውጭ ታጣቂዎች ዝውውር ለመግታት ያለመ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሶርያ ላይ የተጣሉትን የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ለማንሳት የሚወሰዱ አዲስ እርምጃዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ እንዲሁም የአገሪቱ ሕግ እና አሠራሮችን በተመለከተ "ለኢንቨስተሮች የተገዢነት ማብራሪያ" እንደሚያቀርቡ አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል።

በቀድሞው የሶርያ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ለመጣል በአውሮፓውያኑ 2019 የወጣው የሲዛር ሕግ ለ180 ቀናት እንዲታገድ የሚያደርግ ውሳኔ በትራምፕ አስተዳደር እንደሚተላለፍም ተገልጿል።

ትራምፕ፤ ከስብሰባው በኋላ በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት "ሶርያ እጅግ የተሳካላት አገር ሆና መመልከት እንፈልጋለን" ብለዋል።

"የአገሪቱ መሪ ይህንን ሊያደርገው እንደሚችል አምናለሁ። በትክክል አምናለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የሶርያ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ተቋርጦ ቆይቷል። አሁን ግን ሶርያ በዋሽንግተን የሚገኘውን ኤምባሲዋን መልሳ እንድትከፍት ተፈቅዶላታል።

ትራምፕ እና የሶርያው መሪ ሲገናኙ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። ግንቦት ላይ ከ 'ገልፍ ኮኦፕሬሽን ካውንስል' ጉባኤ ጎን ተገናኝተው የነበረ ሲሆን መስከረም ላይ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የእራት ግብዣን ታድመዋል።

በዋይት ሀውስ የተደረገው ጉብኝት ከዚህ ቀደም በጂሃዲስትነት ይታወቁ ለነበሩት ሶርያ መሪ ግዙፍ የገጽታ ለውጥ ነው።

አልሻራ ከጥቂት ዓመታት በፊት የአልቃይዳ ቅርንጫፍ መሪ የነበሩ ሲሆን ኋላ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል። እስከተያዘው አውሮፓውያኔ 2025 ድረስ ሐያት ታሕሪር አል ሻም የተባለው ታጣቂ ኢስላማዊ ቡድን መሪ ነበሩ።

አሜሪካ ይህንን ቡድን በአሸባሪ ድርጅትነት ፈርጃ እንዲሁም መሪው ያለበትን ለጠቆመ ሰው 10 ሚሊዮን ብር ሽልማት አቅርባ ነበር። ከአራት ወራት በፊት ግን የአሸባሪነት ፍረጃው ተነስቷል።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአሜሪካ ግምጃ ቤት አልሻራን "ከልዩ የዓለም አቀፍ አሸባሪነት ዝርዝር" አውጥቷቸዋል።

አልሻራ የሶርያ ፕሬዝዳንት ከሆኑ ወዲህ አገሪቱን መልሶ ለመገንባት እና በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ገጽታ ለማደስ ሲሠሩ ቆይተዋል። ለ13 ዓመታት በተካሄደው ጦርነት የወደመችውን ሶርያ መልሶ ለመገንባት የውጭ ድጋፍ አግኝተዋል።

ትራምፕ፤ "አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል" ሲሉ ስለ ሶርያው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። "አስቸጋሪ ጊዜ ካላሳለፍክ ዕድል አይኖርህም ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።