ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስዊድናዊያን ሴቶች ሥራቸውን እየለቀቁ የቤት እመቤት መሆን የመረጡት ለምንድነው?
ስዊድን በዓለማችን የፆታ እኩልነት በተሻለ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ቢሆንም ሴቶች በገፍ ሥራቸውን እየለቀቁ ይገኛሉ። ለምን?
የ25 ዓመቷ ቪልማ ላርሰን ከዚህ ቀደም በሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ፣ የዕድሜ ባለፀጋዎች መንከባከቢያ እና በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ትሠራ ነበር።
ነገር ግን ሥራዎቿን እርግፍ አድርጋ ትታ ቤት ውስጥ ተቀምጣ ከፍቅር ጓደኛዋ ጋር ትኖራለች። እንዲህ ደስተኛ ሆኜ አላውቅምም ትላለች።
“ሕይወቴ ሰላማዊ ነው። እየተቸገርኩ አይደለም። ይህን ያህልም ጭንቀት የለብኝም።”
በፋይናንስ መስክ የተሠማራው ፍቅረኛዋ ከቤት ነው የሚሠራው። እሱ ኮምፒወተሩ ላይ ሲተከል እሷ ወደ ጂም ትሄዳለች፣ አሊያም ሻይ ቡና ለማለት ትወጣለች ካልሆነ ምግብ ታበስላለች።
ማዕከላዊ ስዊድን ያደጉት ጥንዶቹ አብዛኛውን ጊዜ ለሽርሽር ከሀገር ይወጣሉ። የሚመጣውን የበረዶ ወቅት በቆጵሮስ ለማሳለፍ ወስነዋል።
“በየወሩ ከደሞዙ ይቆርጥልኛል። ካልበቃኝ ጨምረኝ ብዬ ጠይቀዋለሁ። ከምፈልገው በላይ ካለኝ ደግሞ እቆጥባለሁ” ትላለች ላርሰን።
የሕይወት ዘይቤዋን በኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ እና ቲክቶክ ለ11 ሺህ ተከታዮቿ ታካፍላለች። እስከ 400 ሺህ ‘ላይክ’ ድረስ አግኝታ ታውቃለች። ነገር ግን ከማኅበራዊ ሚድያ ገንዘብ እያገኘሁ አይደለም ትላለች።
ሄማፍሩ ማለት በስዊድን ቋንቋ የቤት እመቤት እንደማለት ነው። ራሷን ‘ሶፍት ገርል’ ስትል ትገልፃለች። ሥራ ላይ ከማተኮር ይልቅ የፍቅር ጓደኛ አሊያም ትዳር ይዞ ቤት ውስጥ መዋልን የሚመርጡ ሰዎች የሚጠቀሙበት ቃል ነው።
ይህ የሕይወት ዘይቤ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በመላው ዓለም እየተስተዋለ ያለ ክስተት ነው። ነገር ግን ላለፉት አምስት አስርታት የፆታ እኩልነት እና የገቢ መመጣጠን ለማስከበር ስትጥር በነበረችው ስዊድን ይህ ሐሳብ መንሰራፋቱ አስገራሚ እና አከራካሪ ሆኗል።
ባለፈው ነሐሤ የወጣ አንድ ጥናት ትምህርት ቤት ካሉ ታዳጊ ሴት ተማሪዎች 14 በመቶ ያክሉ ወደፊት ሲያድጉ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ከፍቅረኛ ወይም ከትዳር አጋር መኖርን ይመርጣሉ።
ምንም እንኳ እንደ ቪልማ ላርሰን ያሉ ሥራቸውን እየለቀቁ ያሉ ሴቶች ቁጥርን የሚያሳይ ማስረጃ ባይኖርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህ የኑሮ ዘይቤ መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም።
የስዊድን የፌሚኒስት ፓርቲ መሪ የሆኑት ጉድሩን ስኪማን ሴቶች በፍቅር አጋራቸው ገቢ ላይ ጥገኛ ሆነው መኖራቸው “በጣም አደገኛ ነው” አልፎም የፆታ እኩልነትን “አንድ እርምጃ ወደኋላ የሚጎትት ነው” ይላሉ።
‘ሶፍት ገርል’ የተባለውን የሕይወት ዘይቤ በተለመከተ ስዊድናዊያን በቴሌቪዥን ሳይቀር ክርክር እና ውይይት እያደረጉ ነው።
ስዊድን አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው በዓመት የስድስት ሳምንታት ዓመታዊ እረፍት እንዲሰጡ ታስገድዳለች። በሳምንት ከ50 ሰዓታት በላይ የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር ከ1 በመቶ አይበልጥም።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች በሥራቸውና በሌሎች የሕይወት መስኮች ምክንያት ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው ምናልባት ሥራቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል የሚል ግምት አለ።
ጄን ዚ የሚባለው ከአውሮፓውያኑ 1997-2012 ባለው ጊዜ የተወለደው ትውልድ በማኅበራዊ ሚድያዎች መዝናናትን ሠርቶ ከመለወጥ በላይ ሲያከብር ይስተዋላል።
ወደፊት ልጆች መውለድ የምትፈልገው ቪልማ ላርሰን ሥራ ትታ የቤት እመቤት ለመሆን ከወሰነችባቸው ምክንያቶች አንዱ ዕድሜያቸው የገፋ ሴቶች ሥራ እና የተቀረውን ሕይወት ለማስተሳሰር ሲቸገሩ ማየቷ ነው።
ስዊዲናዊቷ ኢኮኖሚስት ሾካ አርማን ሴቶች ሥራቸውን ትተው ቤት ከተቀመጡ ገንዘብ መቆጠብ እንደማይችሉ፣ ጡረታ እንደማይኖራቸው እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው እንደሚችል ትምህርት በመስጠት ላይ ናት።