"የእባቦች ንግሥት" ተብላ የምትጠራው ኢንዶኔዥያዊት ሐኪም እንዴት ስለ መርዝ ተማረች?

የድንገተኛ አደጋ ሐኪሟ ትሪ ማሃራኒ በሥራ ዘመኗ በርካታ ሞቶችን ተመልክታለች። ከ15 ዓመት በፊት በእባብ ንክሻ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈውን ታካሚ ፊት ግን መችም አትረሳውም።

እድሜው በ30ዎቹ ውስጥ የነበረው የኤሌክትሪክ ባለሙያ አንዴ ነቃ ሲል አንዴ ደግሞ ራሱን ሲስት ከቆየ በኋላ እጇን ጭምቅ አድርጎ ይዞ ሕይወቱን እንድታድን ለመናት። አንድ ዓመት እንኳ ያልሞላው ህጻን ልጅ ያለው ታካሚው እያለቀሰ መሞት እንደማይፈልግ ተናገረ።

"ሆስፒታሉ ውስጥ በርካታ ሐኪሞች ነበርን፤ ሁላችንም ግን ልንረዳው አልቻልንም" ስትል የ54 ዓመቷ ዶክተር ማሃራኒ ታስታውሳለች።

ኢንዶኔዥያ መርዛማ የእባብ ዝርያዎችን በመያዝ ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ብትሆንም አንድም የእባብ ንክሻ ስፔሻሊስት ወይም የሕክምና መመሪያ አልነበራትም።

ዶ/ር ማሃራኒ ይህንን ለመለወጥ ቁርጠኛ ነበረች። በአውሮፓውያኑ 2012 በባዮሜዲካል ሳይንስ ከቤልጂየም የዶክትሬት ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ ስለ መርዞች ጥናት የሚደረግበትን 'ቶክሲኖሎጂ' የተሰኘ ትምህርት ለመማር ወሰነች።

ከዚያም፤ መረጃ ለመሰብሰብ 18,000 ደሴቶችን ይዛ አገር በሆነችው ኢንዶኔዢያ ባሉት ሁሉም ክልሎች ትጓዝ ጀመር። ከአምስት ዓመት በኋላ በአውስትራሊያ ያገኘችውን የቶክሲኖሎጂ ፌሎውሺፕ እድል አጠናቀቀች።

ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በደቡብ ምሥራቅ አገራት ውስጥ በየዓመቱ 135,000 ሰዎች በእባብ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥም 10 በመቶው ለሞት የሚዳርጉ ናቸው።

ዶ/ር ማሃራኒ ግን ቁጥሩ በብዙ ሺዎች ይበልጣል ባይ ነች። በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ለማከም እንደሚሞክሩ ወይም ወደ ባህል ሕክምና እንደሚሄዱ ታስረዳለች።

በእባብ የተነከሱ ሰዎች መርዙን መጥጠው ካወጡ በኋላ ቁስሉ ላይ ሙቅ ውሃ፣ ቀይ ሽንኩርት ወይም ጥቁር ድንጋይ ጭምር ያደርጉበታል። ይህ ዓይነቱ ሕክምና የቲሹ መጎዳት ከፍ ሲልም ሞት ጭምር ያስከትላል።

በእባቦች የሚደርስ ንክሻ ቁጥር ከፍ እያለ ነው። የዚህ ምክንያት ደግሞ በከተሜነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሰዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች የሚላመዱ እባቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ነው።

ኢንዶኔዥያ ውስጥ የእባብ ንክሻ የኅብረሰተብ ጤና ተግዳሮት ብቻ አይደለም። በዓለም ላይ በእባብ በመነደፍ 2.7 ሚሊዮን አደጋዎች በየዓመቱ ይከሰታሉ። ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚከሰቱት በእስያ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ የዓለም የጤና ድርጅት የመርዛማ እባብ ንክሻን ችላ የተባለ ሞቃታማ አካባቢ (tropical) በሽታ ብሎ በማወጅ እንደ ቺኩንጉንያ እና ሊፕረዚ ካሉ በሽታዎች ጋር በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ አስቀምጦታል። በእባብ ንክሻ የሚፈጠርን ሞት እና የአካል ጉዳት ከ2030 በፊት በግማሽ ለመቀነስም አቅዷል።

ዶ/ር ማሃራኒ በኢንዶኔዥያ ክልሎች በምትጓዝበት ወቅት ከአካባቢዎቹ ሆስፒታሎች ጋር መተባበር ጀመረች። የዓለም የጤና ድርጅት የእባብ ንክሻ አስተዳደር መመሪያን በመጠቀምም ለነዋሪዎች እና ሕክምና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠትን ተያያዘችው።

ባህላዊ ልማዶች እና አመለካከቶችን መቀየር ግን ከባድ ነገር ነበር፤ በተለይ ደግሞ አስተማሪዋ ሴት ስትሆን።

"ሰዎች የመርዝ ባለሙያዋ ሴት [ትሆናለች] ብለው አይጠብቁም። ብዙ ሰዎች ስሜን ይጠሩት የነበረው አቶ ማሃራኒ ብለው ነበር" ትላለች። "ማንቋሸሽ ደርሶብኛል፣ ተፈትኛለሁ፣ አልፎ ተርፎም መጥፎ ስሞች ተሰጥተውኛል፤ በተለይ ከእኔ በላይ እንደሚያውቁ በሚያስቡ ወንዶች" ስትል የደረሰባት ትዘረዝራለች።

በፈተና መሃል ብርታት የሰጣት እምነቷ ነበር። "ሁሌም ቢሆን ሥራዬ ሕይወት ማዳን እንደሆነ አስታውሳለሁ።"

"አገሬን ለመርዳት ከፈጣሪ የተሰጠኝ ልዩ ጥሪ ነው" ትላለች።

ከተዛባው ጾታዊ አመለካከት በላይ ፈተና የነበረው ግን የመንግሥት ቸልተኝነት ነው። ኢንዶኔዥያ ውስጥ 80 የሚጠጉ መርዛማ የእባብ ዝርያዎች ቢኖሩም የአገሪቱ መንግሥት የሚያመርተው የሦስት የእባብ ዝርያዎችን መርዝ ለማስወገድ የሚያስችል አንድ ፀረ-መርዝ መድኃኒት ነው።

በተጨማሪም መድኃኒቱ በአራት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት መጠን ውስጥ መቀመጥ አለበት። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ወዳሉ ደሴቶች ማጓጓዝ እና ማከማቸትን አስቸጋሪ ያደርጋል።

በዚህም የተነሳ ኢንዶኔዥያ ፀረ-መርዝ መድኃኒቶችን ከውጭ ታስገባለች። የአንድ ዙር ሕክምና ዋጋም እስከ 4,500 ዶላር ይደርሳል።

ከአምስት ዓመት በፊት አንድ የ12 ዓመት ልጅ በአንድ ያልተለመደ "ኢስተርን ራስል ቫይፐር" ዝርያ እባብ ከተነደፈ በኋላ ራሱን ሳተ። የታዳጊው ሁኔታው በፍጥነት እየተባባሰ ሄዶ ጡንቻዎቹ መላላት እና ኩላሊቶቹም የመበላሸት ምልክት ማሳየት ጀመሩ።

ዶ/ር ማሃራኒ ፀረ-መርዝ መድኃኒት ለመግዛት ወደ ታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ መብረር ነበረባት። ታዳጊው ወደ ለምባታ ደሴት ለመሄድ ደግሞ በሦስት በረራዎችን መሳፈር ነበረባት።

መድኃኒቱን ለመግዛት በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ያወጣችው ዶ/ር ማሃራኒ ገንዘቧ እያለቀ ስለነበር በአውሮፕላን ማረፊያው ወለል ላይ ከመተኛት ውጪ አማራጭ አልነበራትም።

ሁሌም እንደምታደርገው ለታዳጊው መድኃኒቱን የሰጠችው በነጻ ነው። ብዙውን ጊዜ የደመወዟን 90 በመቶ ለታካሚዎቿ ፀረ መርዝ መድኃኒት መግዣነት እንደምታውል እና መልሰው እንዲከፍሏት እንደማይጠይቅ ትናገራለች።

"ጤነኛ ነኝ፤ ሁሌም ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት እችላለሁ። ሕይወቱ እያለፈ ያለ ታካሚ ካለኝ ግን ዋናው አስፈላጊ ነገር ፀረ መርዝ መድኃኒት ማግኘት ነው። ስለዚህ ቅድሚያ መስጠት አለብኝ፤ ቅድሚያ የሚሰጠውም ለሰው ህይወት ነው" ትላለች።

በባህር ዳርቻ ላይ የኮኮናት ውሃ የሚሸጠው የታዳጊው አባል ልጁ ከነቃ በኋላ ትልቅ ኮኮናት ሰጥቷታል። ታዳጊውም ጨርሶ ድኗል።

ዶ/ር ማሃራኒ፤ "ለእኛ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል። እርሱ ግን ያገኘው ብቸኛው ውድ ነገር ይህ ነበር" በማለት ትናገራለች።

አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ጥረቷ ፍሬ አፍርቷል። ለእሷም "የእባቦች ንግሥት" የሚል ቅጽል አስገኝቶላታል።

በ2014 ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን የመሰረተችው 'ዘ ኢንዶኔዢያን ቶክሲኖሎጂ ሶሳይቲ' የተሰኘው ማህበር አሁን ላይ ከ500 በላይ አባላት አሉት። ብዙዎቹም የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው። ከ2015 ጀምሮም የዓለም የጤና ድርጅት አማካሪ ሆና እየሰራች ነው።

የመሰረተችው ማህበር የሚያካሄደው ዘመቻ ሚሊዮኖች ጋር መድረሱን ትናገራለች። ቀላል የሕክምና ሂደት የሆነው፤ የአንድ ሰው በእባብ ከተነከሰ በኋላ ሰውነቱ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ አሰራር በአሁኑ ሰዓት በርካቶች የሚረዱት እውቀት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት እንደ ጃካርታ እና ባሊ ባሉ በርካታ ነዋሪ ያለባቸው አካባቢዎች በብዛት በሚገኘው የጃቫ ኮብራ ለሚደርስ ንክሻ የሚውል አዲስ ፀረ-መርዝ በተሳካ ሁኔታ ማዘጋጀት ችላለች። በቅርቡም የሙከራ ምርት ይጀመራል።

ወታደራዊ ሐኪም ከነበረው ከሟቹ አባቷ ባልደረቦች የበለጠ ግን እርካታ የሚሰጣት ነገር የለም። "ወደ ሩቅ አካባቢ ከመላካቸው በፊት ብዙውን ጊዜ የእባብ ንክሻ ስልጠና እና ፀረ-መርዝ ለማግኘት ወደ ቤቴ ይመጣሉ" ትላለች።

ዶ/ር ማሃራኒ ህልም በሂደት የአገሪቱን የመጀመሪያ የቶክሲኖሎጂ ክሊኒካል ትምህርት ቤት መመስረት እና መንበሯን ለአዲሱ ትውልድ ሐኪሞች ማስተላለፍ ነው።