ሊነድፈው የነበረ ኮብራ እባብን ነክሶ የገደለው ሕንዳዊ ሕጻን

በሕንድ የአንድ ዓመት ሕጻን መርዘኛ እባብ ነክሶ መግደሉ ከተሰማ በኋላ የአገሬው ሰው ወሬውን ተቀባብሎታል።

ሕጻኑ ጎቪንድ ኩመር ይባላል።የሚኖረው ሕንድ ከኔፓል ጋር በምትዋሰንበት ግዛት አቅራቢያ ነው።

እአአ ሐምሌ 24/2025 በምሥራቃዊ ሕንድ ቢሃር ግዛት ውስጥ በሞህቺ ባንካታዋ መንደር ውስጥ በሚገኘው የቤተሰቡ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እየተጫወተ ሳለ ነው እባቡን ያገኘው።

ጎቪንድ እባቡን ከመጫወቻ አሻንጉሊት ለይቶ አልተመለከተውም።ከዚያም በእጆቹ አፈፍ ሲያደርገው፣ እባቡም በእጆቹ ላይ መጠምጠሙን የጎቪንዳ አያት ይናገራሉ።

ሁሉን ነገር ወደ አፉ የሚወስደው ሕጻኑ ጎቪንድ፣ እባቡን ክፉኛ ነከሰው። ምንም እንኳ በንክሻው እባቡ ቢሞትም ጎቪንድም ተጎድቷል።

የጎቪንድ አያት ማቲሳሪ ዴቪ "እናቱ የጓሮ አትክልቶቹ ውስጥ ተፍ ተፍ ትል ነበር" ይላሉ። አክለውም "እባቡን ያዘና በጥርሶቹ ነከሰው። ከዚያም ኮብራ እባብ መሆኑን አስተዋልን" ሲሉ ሁኔታውን ለመገናኛ ብዙኃን አስረድተዋል።

በቅጽበት ውስጥ ጎቪንድ ራሱን በመሳቱ ቤተሰቡ ሕጻኑን አንከብክቦ በአካባቢው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ሆስፒታል ወሰዱት።

በቢሃር ዋና ከተማ ቤቲያህ በሚገኘው የመንግሥት ሕክምና ኮሌጅ ጎቪንድን ያከሙት ዶ/ር ኩመር ሳራብህ "ሕፃኑ እኛ ጋር ሲደርስ ፊቱ፣በተለይ አፉ አካባቢ አብጦ ነበር" ብለዋል ።

በዕለቱም ከጎቪንድ በተለየ በእባብ የተነደፈውን ሌላ ሕፃን ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን አስታውሰው፣ሁለቱም ልጆች አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር ሳራብህ በእባብ መነደፍም ሆነ እባብን መንከስ ለሰው ልጆች ጎጂ ቢሆኑም፣ አንዱ ግን የበለጠ አደገኛ መሆኑን ያስረዳሉ።

"እባብ ሰውን ሲነድፍ መርዙ ወደ ደማችን ውስጥ በቀጥታ ይገባል እና የነርቭ ስርዓታችን ላይ ተጽእኖ 'ኒውሮቶክሲሲዝም' ያስከትላል። ይህ ደግሞ ለሞት ሊዳርግ ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሳውራህ አክለውም "አንድ ሰው እባብ ሲነክስ ግን መርዙ በቀጥታ የሚገባው ወደ የምግብ መፍጫ ስርዓታችን ነው። ይህም አካላችን መርዙን አክሽፎ እንዲያስወግደው ያደርጋል" በማለት በልጁ ጨጓራ ውስጥ ቁስለት ወይም መድማት እስከሌለ ድረስ ውጤቱ የከፋ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።

ሕንድ ወደ 300 የሚጠጉ የእባቦች ዝርያዎች መገኛ ስትሆን ከ60 በላይ የሚሆኑት በጣም አደገኛ ከሚባሉት መካከል ናቸው።

አገሪቱ "የዓለማችን የእባብ ንድፊያ ዋና ከተማ" በሚል ቅጽል ስም ትታወቃለች።

ከሰኔ እስከ መስከረም ወር ድረስ በሚቆየው ዝናባማ ወራት ወቅት ደግሞ በእባብ ተነድፈው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል።

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ81,000 እስከ 138,000 የሚደርሱ ሰዎች በእባብ ተነድፈው እንደሚሞቱ ይናገራል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2000 እና 2019 መካከል በሕንድ በዓመት በአማካይ 58,000 ሰዎች በእባብ ተነድፈው መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ በእባቦች ተነድፈው የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር አሁንም በስፋት አይዘገብም።

የሕንድ ጤና እና የቤተሰብ ደህንነት ሚኒስቴር ለዚህ ምክንያቱ ሲያስረዳ እነዚህ ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አዳጋች ነው ብሏል።