ትራምፕ የቀረቡባቸውን ክሶች ለመከላከል ደጋፊዎቻቸው 40 ሚሊዮን ዶላር ማውጣታቸው እያነጋገረ ነው

Donald Trump

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዚህ ዓመት ብቻ ለሕግ ጉዳዮች ወጭ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማውጣታቸው ተነግሯል።

ይህ ገንዘብ የወጣው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረቡባቸውን ክሶች ለመከላከል ነው።

ትራምፕ የሚቀርብባቸው ክስ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ወጪውም በዚያው ልክ ይጨምራል።

ሰነዶችን በመሰወር፣ መረጃን ለመደበቅ ሰዎችን በገንዘብ ዝም በማሰኘት እና በስም ማጥፋት ወንጀል ተከሰዋል።

በሌላ በኩል የፌደራል የፍትህ መሥሪያ ቤት ደግሞ የ2020 ምርጫን ለመቀልበስ አሲረዋል በሚል ክስ እንደሚመሰርትባቸው ይጠበቃል።

የትራምፕ ደጋፊዎች ግን ዕጩ ተፎካካሪያቸውን ለመከላከል የሚያደርጉት ድጋፍ ሕጋዊ እና ተገቢ መሆኑን እየገለጹ ነው።

ደጋፊዎ ችእንደሚሉት ዘመቻው የተለያዩ ሰዎችን እና ድርጅቶችን ያካተተ ሲሆን “ሕጋዊ ያልሆነ ማሸማቀቅን መከላከል ነው” ብለውታል።

ድጋፉ የሚደረገው ራሳቸው ዶናልድ ትራምፕ በመሰረቱት ሴቭ አሜሪካ በተባለ የገቢ አሰባሳቢ ድርጅት አማካኝነት ነው።

ይህ ድርጅት ሰዎች የሕግ ጉዳይ ወጭን መሸፈን በተሳናቸው ጊዜ ድጋፍ በማድረግ የቤተሰብን ሕልውና ማስቀጠል ዓላማው እንደሆነ ይገልጻል።

አሁን ለትራምፕ ወጭ ያደረገው 40 ሚሊዮን ዶላር ግን ድርጅቱ በአጠቃላይ ለ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ካወጣው ይበልጣል።

ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመጭበርበሩ ደጋፊዎቻቸው ሴቭ አሜሪካ ላይ እየለገሱ እንዲደግፏቸው ገልጸው ነበር።

በዚህ ሂደትም ባለፈው ዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር የሰበሰቡ ሲሆን 16 ሚሊዮን ብቻ ለሕጋዊ ወጭዎች አውለዋል።

10 ሚሊዮን ደግሞ ለግል ወጪያቸው ተጠቅመዋል። የእርሳቸው ዘመቻ እና የደጋፊዎቻቸው ልገሳ ማጭበርበር ስለመፈጸማቸው የተደረገ ምርመራ የለም።

የ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተጀመረበት ወቅት ዶናልድ ትራምፕ አንድም ሳንቲም ላለማባከን ቃል ገብተው ነበር።

ነገር ግን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከእያንዳንዱ መዋጮ 10 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ አውለውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የምርጫ ቅስቀሳ የፋይናንስ ሙያተኛ የሆኑት ጃሰን ቶርችንስኪ እንደሚሉት ትራምፕ ከእርዳታ የሚያገኙትን ገንዘብ በቀጥታ ለሕግ ወጪ በመጠቀማቸው የምርጫ ሕጉን ሳይጥሱ እንዳልቀሩ ይገልጻሉ።

”የምርጫ ቅስቀሳ ኮሚቴ የሕግ ጉዳይ ወጭን መሸፈኑ የማይጠበቅ አይደለም” ያሉት ቶርቺንስኪ፣ “ችግሩ ግን ትራምፕ ወጪያቸውን ሦስተኛ ወገን የሚሸፍንላቸው የፌደራል እጩ ናቸው፣ የፌደራል ኮታን ያለፈ የገንዘብ ልገሳ ግን ብዙ ነገር ሊያስነሳ ይችላል” ብለዋል።

የቅድመ ምርጫ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል በ2024 ዕጩ ሆነው ይቀርባሉ። ነገር ግን አንዳንድ ተቃዋሚዎቻቸው የ2024 ወጪያቸውን እየተቃወሙ ነው።

በእርግጥ ደጋፊዎቻቸውም አሁንም የትራምፕን የሕግ ወጪ ሕጋዊነት በማብራራት እየተከራከሩላቸው ነው።

የትራምፕ የተጋነነ ወጪ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ውጥረት ውስጥ እንዳስገባው የሚያሳዩ የተወሰኑ መረጃዎች አሉ።

እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ከሆነ ትራምፕን ለሚደግፍ ሌላ ቡድን የለገሰው 60 ሚሊን ዶላር እንዲመለስለት ሴቭ አሜሪካ ጥያቄ አቅርቧል።

ነገር ግን ገንዘቡ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ስለመመለሱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካ ብዙሃን መገናኛዎች እንደዘገቡት ደግሞ የትራምፕ አማካሪዎች ለሕግ ጉዳዮች ብቻ የሚሆን ወጪ ለመሰብሰብ የተለየ መንገድ እየፈለጉ ነው።

የምርጫ ቅስቀሳ የፋይናንስ ሙያተኛው ቶርቺንስኪ እንደሚሉት እንደዚህ አይነት የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች የተሰበሰበውን ገንዘብ መጠን እና ገንዘቡ የሚውልበትን ዓላማ የማሳወቅ ግዴታ የለባቸውም።

ብዙ ክሶች መቅረባቸውን ስለሚቀጥሉ “የሕግ ጉዳዮች ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር እጠብቃለሁ” የሚሉት ትርቺንስኪ፤ “በዓመቱ መጀመሪያ አጋማሽ 40 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በሚቀጥለው ስድስት ወር ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ቢያድግ አያስደነግጠኝም” ብለዋል።