ሁለት ልጆቿን "ወደ ገነት ልኬያለሁ" በሚል የገደለችው እናት የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈረደባት

ጄጄ እና ታይሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ዱምስደይ' (የዓለም መጨረሻ) የተባለው እምነት ተከታይ የሆነችው የአሜሪካዋ አይዳሆ ግዛት ነዋሪ ሁለት ልጆቿን ከገደለች በኋላ የባሏን የቀድሞ ሚስት ለመግደል በማሴር ጥፋተኛ ሆና የተገኘችው እናት ዕድሜ ልክ ተፈረደባት።

የ50 ዓመቷ ሎሪ ቫሎው ደይቤል በመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል እና ለመግደል በማሴር ወንጀል ጥፋተኛ ሆና ተገኝታለች።

ቫሎው ጄጄ የተባለውን የሰባት ዓመት ወንድ ልጇንና ታይሊ ራያን የተሰኘች የ16 ዓመት ሴት ልጇን ገድላለች።

የልጆቹ ሬሳ በ2020 ቻድ ደይቤል በተባለው ባሏ ቤት ውስጥ ነው የተገኘው።

ሰኞ ዕለት ዳኛ ስቲቨን ቦይስ ተከሳሿን ለግድያው ወንጀል ለሶስት ተከታታይ ጊዜ በፅኑ የዕድሜ ልክ እሥራት ቀጥተዋታል።

በፍርድ ሂደቱ የልጆቹ ዘመዶች ስሜት የሚነካ አስተያየታቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል።

ቻድ ደይቤል የተባለው ግለሰብም በልጆቹ ግድያ የተከሰሰ ሲሆን ቫሎውን ከማግባቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሞተችው የቀድሞው ሚስቱ ግድያም ተከሷል።

የሰውየው የፍርድ ሂደት ለሚቀጥለው ዓመት ቀጠሮ ተሰጥቶበታል።

ፀሐፊው ደይቤል በሞርሞን እምነት አስተምህሮት ላይ ያተኮሩ የዓለም ፍፃሜን የሚዘክሩ በርካታ ልብ-ወለዶች ፅፏል።

ቫሎው እና ደይቤል ለዓለም ፍፃሜ ለመዘጋጀት ባለመ አንድ ንቅናቄ አማካይነት ሳይገናኙ እንዳልቀረ ተነግሯል።

በ2019 መገባደጃ ቫሎው፤ ጄጄ እና ታይሊ የተባሉት ልጆቿን ይዛ ወደ አይዳሆ ግዛት ወደ ደይቤል ቀረብ ብላ መኖር ትጀምራለች።

ሴትየው ወደ አይዳሆ በሄደች በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የደይቤል የቀድሞ ሚስት ትሞታለች።

ታኅሣሥ 2019 በወጣ የሬሳ ምርመራ ታሚ የተባለችው የሰውየው የቀድሞ ሚስት ተመርዛ እንደሞተች ያሳያል።

ይሄኔ ነው የጄጄ አያቶች ለፖሊስ ደውለው የሰባት ዓመቱ ልጅ ልጃቸው ደኅንነት እንዲጣራላቸው የጠየቁት።

ከአያቶቹ ጥሪ በኋላ ፖሊስ ፍለጋውን ቢያጧጡፍም ጄጄ እና ታይሊ ሊገኙ አልቻሉም።

ልጆቹ የት እንደገቡ ባለመታወቁ ፖሊስ በመላው ሃገሪቱ ፍለጋውን ይቀጥላል።

ቫሎው ልጆቼን አልገደልኩም ስትል ታስተባብላለች።

ሰኞ ዕለት ለፍርድ ቤቱ፤ እየሱስን እንዳናገረችውና ልጆቿና ታሚ ገነት ውስጥ “ደስተኛ ሆነ እየኖሩ እንዳለ” መስማቷን ተናግራለች።

“እየሱስ ክርስቶስ ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ እንዳልተገደለ ያውቃል” ትላለች ቫሎው።

አክላም የሶስቱ ሟቾች መንፈስ እንደጎበኛትና “ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈፀመች” እንደነገሯት ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች።

የጄጄ ሴት አያት ኬይ ዉድኮክ “ሴትየዋ ሰይጣን ናት፤ ለፈፀመችው አስከፊ ድርጊት ኃላፊነት መውሰድም ሆነ ምንም ዓይነት ቁጭት የማይታባት ሴት ናት” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ዱምስደይ ከልት የተሰኘው እምነት ዓለም ትጠፋለች ብለው የሚቀበሉ ሰዎች ስብስብ ሲሆን ምድርን ቀድመው ማጥፋት እንዳለባቸውም ያምናሉ።