በዩኬ የተነሳውን 'የጸረ-ስደተኞች' ነውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ

በዩናይትድ ኪንግደም በሳምንቱ መጨረሻ የተባባሰው ጸረ-ስደተኛ ተቃውሞ ሊረግብ ባለመቻሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪየር ስታርመር ካቢኔያቸው አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ።

ጸረ-ሙስሊምና ጸረ- ስደተኛ መልክ እየያዘ የመጣው አመጽ ዜጎች እና ንብረተ ላይ ጉዳት አድርሷል።

ፖሊስ 150 ቀኝ አክራሪ ነውጠኞችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።

ሮተራም በምትባለው የዩኬ ከተማ ጸረ-መጤ ነውጠኞች፣ ስደተኞች አርፈውበታል በሚባል ሆቴል ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ይህን ተከትሎ ሰር ኪየር ስታርመር ድርጊቱን ኮንነዋል።

ከሮተራም ሌላ በታምዎርዝ፣ ሚድልቦሮ እና ሮተርሃም ትናንት እሑድ ነውጡ አይሎ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦዘኔ ያሏቸውን ነውጠኞች ለሕግ እንደሚያቀርቡ ዝተዋል።

ዛሬ ሰኞ ሰር ኪየር ስታርመር የጠሩት ድንገተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ካቢኔያቸውን ጨምሮ ደኅንነትና ፖሊስን የሚያካትት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስተር ሰር ስታርመር ትናንት እሑድ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር በጸረ-ስደተኞች አመጽ ውስጥ የተሳተፉ ሁሉ ከመጸጸታቸው በፊት እጃቸውን እንዲሰበስቡ እመክራለሁ ብለዋል።

“በአገራችን ዩኬ ሁሉም ሕዝብ ደኅንነቱ ተጠብቆ ይኖራል። ይሁንና ሙስሊሞች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። መስጊዶች አደጋ እየደረሰባቸው ነው፤ ሌሎች አናሳ ማኅበረሰቦችም ስጋት ላይ ናቸው፣ የናዚ ሰላምታ በየጎዳናው እየታየ ነው። ፖሊስ ተደብድቧል። ይህ የአደገኛ ቦዘኔነት ድርጊት ነው። ይህ ነውረኛ ድርጊት በስሙ ለመጥራት አላፍርም፤ ይህ የቀኝ አክራሪዎች የአደገኛ ቦዘኔነት ተግባር ነው” ብለዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ለመስጊዶች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ አዟል። ምዕመናን ወደ መስጊዶቻቸው በፍጥነት እንዲመለሱም እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።

ይህ በዩኬ የተነሳው አመጽ መነሻ የዛሬ ሳምንት ሰኞ በሳውዝፖርት ከተማ አንድ የ17 ዓመት ልጅ በስለት ጥቃት ሦስት ሴት ልጆችን ከገደለ በኋላ ነው።

ትናንት በሮተራም በነበረው ‘ስደተኞች አገራችንን ለቀው ይውጡ’ በሚል ተቃውሞ በትንሹ 10 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ነውጠኞቹ ስደተኞች አሉበት የተባለውን 'ሆሊዳይ ኢን ኤክስፕረስ ሆቴልን' መስታወት በማድቀቅ እሳት ለቀውበታል።

አንድ የፖሊስ አባል ጭንቅላቱን በመመታቱ ራሱን ስቶ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

ፖሊስ እንዳለው በሆቴሉ የነበሩ ስደተኞች ከፍተኛ ስጋት ገብቷቸው ቢቆዩም የከፋ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

በቦልተን በነበረ ተመሳሳይ ተቃውሞ ጸረ ሙስሊምና ጸረ ስደተኛ አቋም ያላቸው የቀኝ አክራሪዎች አደባባይ ቢወጡም 300 በሚሆኑ ጭምብል ባጠለቁ ሙስለሊም እንደሆኑ በሚገመቱ ዜጎች ተቃውሞ ደርሶባቸዋል።

ሙስሊሞቹ “አላሁ አክበር” እያሉ በጸረ ስደተኛ አክራሪዎች ላይ ሲዝቱ ታይተዋል።

ተመሳሳይ ጸረ-ስደተኛ ተቃውሞዎች በቤልፋስት፣ ሳውዝፖርት፣ ሊቨርፑል፣ ኖቲንግሐም፣ ሰንደርላንድ እና ሌሎች በርካታ የዩኬ ከተሞች ላይ ተስፋፍቷል።