የእስራኤል ወታደሮች እጃቸውን ሊሰጡ የነበሩ ሁለት ፍልስጤማውያንን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በወረራ በያዙት ዌስት ባንክ እጃቸውን ሊሰጡ የመጡ ሁለት ፍልስጤማውያን ተኩሰው ሲገድሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ።
ድርጊቱ የተከሰተው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በጄኒን ከተማ በቀጠለበት ወቅት ነው።
የፍልስጤም አስተዳደር የእስራኤል ወታደሮችን "የጦር ወንጀል" ፈጽመዋል ሲል የከሰሰ ሲሆን ግድያውንም "አሰቃቂ" ብሎታል።
የእስራኤል ጦር እና ፖሊስ ግለሰቦቹ "ከሽብር ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው" በሚል የሚፈለጉ መሆናቸውን ገልፀው ክስተቱ እየተገመገመ ነው ብለዋል።
የእስራኤል የቀኝ አክራሪ ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር በግድያው ላይ ለተሳተፉ የጦር አባላት ሙሉ ድጋፋቸውን በመስጠት "አሸባሪዎች መሞት አለባቸው" ብለዋል።
ቪዲዮው ሁለት ፍልስጤማውያን እጃቸውን ወደ ላይ አድርገው ከሕንጻ ሲወጡ ያሳያል።
በበርካታ የእስራኤል ድንበር ጠባቂዎች ተከበዋል። ከዚያም መሬት ላይ እንዲንበረከኩ ተደርጓል። ከመካከላቸው አንዱ መሣሪያ አለመታጠቃቸውን ለማሳየት የለበሰውን ቲሸርት ከፍ አድርጓል።
ከጥቂት ቆይታ በኋላ የፀጥታ አባላቱ ወደ ሕንፃው ተመልሰዋል። ከዚያም የድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ተኩስ ከፍተው ፍልስጤማውያኑን ገደሏቸው።
የመከላከያ ኃይል እና ፖሊስ በጋራ በሰጡት መግለጫ የፀጥታ አካላት ተቀጣጣይ ነገር በመወርወር እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ በመተኮስ "የሽብር ተግባር" በመፈጸም የተጠርጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንን አስታውቋል።
"ኃይሉ ወደ አካባቢው በመግባት ተጠርጣሪዎቹ የሚገኙበትን ሕንጻ በመክበብ ለብዙ ሰዓታት እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ ሲጥር ነበር" ሲል መግለጫው ገልጿል።
"ሕንጻው እንዲከፈት ከተደረገ በኋላ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ለቀው ወጥተዋል። መውጣታቸውን ተከትሎም ተጠርጣሪዎቹ ላይ ተኩስ ተከፍቷል።"
ቤን ጊቪር በኤክስ ገጻቸው ላይ "ተዋጊዎቹ እንደሚጠበቀው እርምጃ ወስደዋል" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር በጄኒን የሚያካሄደው ለወራት በዌስት ባንክ ከተሞች የጀመረው ዘመቻ አካል ነው።
እስራኤል ዘመቻው በጦሯ ላይ እና በኤእሁድ ሰፋሪዎች ላይ ትቃት የሚፈጽሙ ታጣቂዎችን ለመከላከል አስፈላጊ ነው ትላለች።
ረቡዕ ዕለት የእስራኤል ጦር በአቅራቢያው በምትገኘው ቱባስ ከተማ ይህንኑ ዘመቻ ጀምሯል።
እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የምትፈጽመውን ጥቃት ሐማስ በ2016 ዓ.ም. የወሰደውን ጥቃት ተከትሎ ተባብሰው ቀጥለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል ወታደሮች ወይም ሰፋሪዎች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዌስት ባንክ የታጠቁ ቡድኖችን እና ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ከ1,000 በላይ ፍልስጤማውያንን ገድለዋል ብሏል።
እስራኤል በበኩሏ በፍልስጤም ጥቃት ወይም በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት ወታደሮችን እና ሰላማዊ ዜጎችን ጨምሮ ቢያንስ 44 እስራኤላውያን ተገድለዋል ትላለች።















