ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የበለጸጉ አገራት ከአፍሪካ የሚመለምሏቸው ነርሶች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተገለጸ
የበለጸጉ አገራት ከአፍሪካ የሚመለምሏቸው ነርሶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን የዓለማችን ትልቁ የነርሲንግ ቡድን አስታወቀ።
ምልመላውንም “ከቁጥጥር ውጭ” ሆኗል በሚል ነው የቡድኑ መሪ የገለጹት።
ከአፍሪካ ወደበለጸጉ አገራት የሚያመሩ ነርሶችም ቁጥር በመጨመሩ እንደ ጋና ያሉ አገራትን የጤና ስርዓት ስጋት ላይ ጥሎታል።
የጋና ነርሶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ማቅናታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የጤና ስርዓት እየተሽመደመደ እንደሆነ ቢቢሲ መረጃዎችን አግኝቷል።
በርካታ ነርሶች ምዕራባዊ አፍሪካዊቷን አገር ለቀው ለተሻለ ክፍያ ወደ ውጭ አገራት ሄደዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የወጣ መረጃን ስናይ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑ የጋና ነርሶች የዩኬን የነርሲንግ ተቋም ተቀላቅለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ያሉትን ክፍት ቦታዎችን ለመሙላት ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ያሉ ሰራተኞችን ለመመልመል ማማተሩን ቀጥሏል።
ምንም እንኳን ዩናይትድ ኪንግደም በጋና ቀጥተኛ ምልመላን እያደረገች ባይሆንም ነርሶች በኤንኤችኤስ ያሉ የስራ ማስተዋወቂያዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መመልከትም ይችላሉ። ከዚያም ለስራዎቹ ማመልከት ይችላሉ።
የጋና አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታ በርካታ የጤና ባለሙያዎችን ለተሻለ ህይወት ወደ ውጭ አገራት እንዲያዩ እየገፋቸው ነው።
እንደ ጋና ካሉ አገራት እየጎረፉ ያሉ ነርሶች ቁጥር አሳሳቢ መሆኑንም ነው የዓለም አቀፉ የነርሶች ምክር ቤት ሰራተኛ ሃዋር ካትተን የሚናገሩት።
“በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዋነኝነት ስድስት ወይም ሰባት የበለጸጉ ሃገራት ከፍተኛ የነርሶችን ምልመላን የጤና ስርዓታቸው ደካማና ተጋላጭ በሆኑ አገራት እያካሄዱ ነው። ይህም ሁኔታ የአገራቱን የጤና ማዕከላትን ባዶ እያደረጋቸው ነው” ብለዋል።
የግሬተር አክራ ሆስፒታል የነርሲንግ ኃላፊ ጊፍቲ አርዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተቋሙ የጽኑ እንክብቤ ማዕከል ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 20 ነርሶችን አጥቷል። እነዚህ ነርሶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ አቅንተዋል። ነርሶች አገራቸውን ለቀው ወደነዚህ አገራት የመሄዱ ሁኔታ የከፋ ሁኔታዎችን ሊያስከትልም እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
“የህመምተኞን ቁጥር እየቀነስን ነው። በጤና ማዕከላችን መዘግየቶች እያጋጠሙን ነው። ለወደፊቱ የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍለን የህመምተኞች ሞት ሊያጋጥመን ይችላልም” ሲሉ ተናግረዋል።