ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን እና የእስራኤል ግጭት መባባሱን ተከትሎ ትራምፕ የቡድን 7 ጉባኤን አቋርጠው ወጡ
የኢራን እና የእስራኤል ግጭት ተባብሶ አምስተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ እየተካሄደ ያለውን የቡድን 7 ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት አቋርጠው መመለሳቸው ተገለጸ።
በኢራን እና በእስራኤል መካከል እየተባባሰ ከመጣው ግጭት ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ዋሽንግተን መመለስ አለባቸው ሲል ዋይት ሐውስ አስታውቋል።
"ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ቀደም ብዬ መመለስ አለብኝ" ሲሉ ትራምፕ የተናገሩ ሲሆን የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል።
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን "የመከላከል አቅም ለማሳደግ" ወደ ቀጣናው ተጨማሪ መሳሪያ እንደምታሰማራ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት ተናግረዋል።
ነገር ግን አሜሪካ፤ እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸመች ያለችውን የማጥቃት ዘመቻ ልትቀላቀል ትችላለች የሚሉ አስተያየቶችን የአሜሪካ ባለስልጣናት ውድቅ አድርገዋል።
በአሜሪካ እና በዩናይትድኪንግደም መካከል የተደረገውን የንግድ ስምምነት ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን በማሳካት ትራምፕ በጉባኤው ስኬታማ ቀን እንደነበራቸው ለማጉላት ሞክሯል።
ነገር ግን የፕሬዚዳንቱ የፕሬስ ሴክሬታሪ ሰኞ ምሽት "በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄዱ ባሉ ጉዳዮች" ምክንያት ትራምፕ የቡድን ሰባት መሪዎች በካናዳዋ ካናናስኪስ እያደረጉ ያሉትን ጉባኤ አቋርጠው እንደሚመለሱ ተናግረዋል። ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።
ፕሬዚዳንቱ ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት ቀድመው በመሄዳቸው ምክንያት ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እና ከሜክሲኮው ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሺንባ ጋር ለማክሰኞ ታቅዶ የነበረው ውይይት አይካሄድም።
ሰኞ ዕለት በነበረው የፎቶ ፕሮግራም ትራምፕ ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸው "ለትልቅ ጉዳይ" መሆኑን ተናግረዋል።
ትራምፕ ጉባኤውን ሳያጠናቅቁ የሚመለሱት የእስራኤል እና ኢራን እርስ በርስ የሚያደርጉት ጥቃት አምስተኛ ቀኑን በያዘበት ዕለት ነው።
ትራምፕ ቀደም ብለው ትሩዝ ሶሻል በተሰኘ የሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ኢራን በቅርቡ በተካሄደው የአሜሪካ እና የኢራን የኒውክሌር ድርድር ላይ ያቀረቡትን ስምምነት መፈረም እንደነበረባት አስፍረዋል።
"ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ ሊኖራት አይችልም። ደጋግሜ ተናግሬዋለሁ" ብለዋል
ትራምፕ በተጨማሪም 17 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከሚኖሩባት የኢራኗ መዲና "ቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ብዙም ሳይቆይ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በቴህራን ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መነሳቱን ዘግበዋል።
እስራኤል በቀጥታ ሲተላለፍ የነበረው የኢራን የመንግሥት ብሮድካስት ላይ ጥቃት አድርሳ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ካደረገች ከሰዓታት በኋላ ከበድ ያለ ጥቃት ፈጽማለች።
በእስራኤል ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ በቴልአቪቭ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያዎች የተሰሙ ሲሆን የኢራን ሚሳኤሎች ወደ እስራኤል ተወንጭፈዋል።
በዋናነት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚገኙበት የቡድን 7 አገራት መሪዎች ትራምፕ ጉባኤውን ሳያጠናቅቁ ቀድመው መሄዳቸውን እንደሚረዱት ገልጸዋል።
"አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የምታስችል ከሆነ ይህ በጣም ጥሩ ነው" ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገልጸዋል።