ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል የኢራኑን የበላይ መሪ ለመግደል የነበራትን እቅድ ትራምፕ ውድቅ ማድረጋቸው ተሰማ
የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኼሜኒን ለመግደል የነበራትን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ሦስት ባለስልጣናት ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ገለፁ።
እንደ አንድ ባለስልጣን መረጃ ከሆነ ትራምፕ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ኼሜኒን መግደል "ጥሩ ሀሳብ አይደለም" ሲሉ ነግረዋቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ መረጃ ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።
በሁለቱ መሪዎች መካከል ውይይቱ የተካሄደው እስራኤል በኢራን ላይ አርብ ጥቃት ከከፈተች በኋላ ነው ተብሏል።
ኔታንያሁ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ትራምፕ አያቶላህን ለመግደል የነበራቸውን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ሮይተርስ መዘገቡን ቢጠየቁም በቀጥታ ከማረጋገጥ ወይም ከማስተባበል ተቆጥበዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር "በፍፁም ያልተከሰቱ ሀሰተኛ የውይይት መረጃዎች አሉ እና ወደዚያ መግባት አልፈልግም" ብለዋል።
"ነገር ግን ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን ብዬ እንደማስብ ልነግርህ እችላለሁ፤ እኛ ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን እናም አሜሪካም ለዩናይትድ ስቴትስ የሚጠቅመውን ታውቃለች እና እኔ ወደ እሱ አልገባም።"
አንድ የእስራኤል ባለስልጣን ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት "በመርህ ደረጃ" እስራኤል "የፖለቲካ መሪዎችን አትገድልም። እኛ ትኩረታችን በኒውክሌር እና በወታደራዊ ተቋማት ላይ ነው። ስለ እነዚያ ፕሮግራሞች ውሳኔ የሚሰጥ ማንም ሰው በነፃነት እና ያለ ምንም ተጠያቂነት መሆን አለበት ብዬ አላምንም" ብለዋል።
እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢራን የኒውክሌር መሠረተ ልማት እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረችው ባለፈው ሳምንት አርብ ነው።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አገራት መጠነ ሠፊ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ ጥቃቱ እሁድ ዕለት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።
ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ስለመጣው ግጭት በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ "ኢራን እና እስራኤል ስምምነት ማድረግ አለባቸው" ካሉ በኋላ፣ ሁለቱን አገራት ግጭቶችን እንዲያቆሙ እንደሚያደርጉ ሲገልፁ በቅርቡ ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩትን አገራት በመጥቀስ "ልክ ሕንድ እና ፓኪስታንን እንዳስማማሁት ሁሉ" ብለዋል።
ትራምፕ በካናዳ ወደ ሚካሄደው የቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸው አገሪቱ በኢራን ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም ጠይቀው እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
የአሜሪካ እና የኢራን ስድስተኛ ዙር የኒውክሌር ድርድር እሁድ ዕለት ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የአሸማጋይዋ የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሰይዲ መሰረዙን አስታውቀዋል።
ኢራን ለኳታር እና ኦማን በእስራኤል ጥቃት እየተፈጸመባት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለመደራደር ዝግጁ እንዳልሆነች መናገሯን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት፤ አሜሪካ "በኢራን ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት የላትም" ብለዋል።
"በማንኛውም መንገድ፣ ዓይነት ወይም ሁኔታ በኢራን ጥቃት ከደረሰብን፣ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ከዚህ በፊት አይታው በማታውቀው ደረጃ በሙሉ ኃይል እና ጥንካሬ እርምጃ ይወስዳል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።