ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው የታዩት ባይደን በፕሬዝዳንታዊ ፉክክሩ እንዲገፉበት በቤተሰቦቻቸው ተጠይቀዋል ተባለ

ባይደን እና ትራምፕ በምርጫ ክርክር ወቅት

ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የምርጫ ክርክር ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው የታዩት ያደረጉትን ጆ ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚደረግባቸውን ጥሪዎች ችላ እንዲሉ ቤተሰቦቻቸው መናገራቸው ተገለጸ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሑድ ከዘመዶቻቸውጋር ያሳለፉት ባይደን በምርጫው ትግላቸው እንዲቀጥሉ እና ከፉክክሩ እንዳያፈገፍጉ እንደተነገራቸው የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

በአትላንታ የተካሄደውን የምርጫ ክርክር ተከትሎ ባይደን ቃላቶች እየጠፏቸው ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው መታየታቸውን ተከትሎ የፓርቲው ደጋፊዎች ጭንቀት ገብቷቸዋል።

ከምርጫ ክርክሩ በኋላ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ከ81 ዓመቱ ባይደን ዕድሜ ጋር በተያያዘ ያለው ስጋት ጨምሯል።

እሑድ ዕለት የተለቀቀው የሲቢኤስ ኒውስ/ዩጎቭ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው ከሆነ 72 በመቶው መራጮች ባይደን ፕሬዝዳንት ሆነው ለማገልገል የአእምሮም ሆነ የማገናዘብ ተመጣጣኝ አቋም የላቸውም ብለው ያምናሉ። ከዴሞክራቲክ ፓርቲ መራጮች መካከል ግማሽ ያህሉ ከፉክክሩ መውጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ባይደን ከምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ያገኙት መልዕክት ትራምፕን ለማሸነፍ የሚችሉት የፓርቲው ትክክለኛ ሰው ሆነው መቀጠላቸውን ነው።

ሜሪላንድ በሚገኘው የካምፕ ዴቪድ በተደረገው የቤተሰብ ስብሰባ የባይደን ባለቤት ጂል፣ ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ተገኝተውበታል።

ጂል ባይደን ከቮግ መጽሔት ጋርበስልክ ባደረጉት ቆይታ “እነዚያ የምርጫ ፉክክሩ የ90 ደቂቃዎች ክርክር የፕሬዚዳንትነቱን አራት ዓመታት አጠቃላይ ሁኔታ ማጠቃለል የለባቸው” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትግሉን ይቀጥላሉ ከማለት ባለፈ ባለቤታቸው “ሁልጊዜም ለአገር የሚበጀውን ያደርጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ቤተሰቡ በምርጫው እንዲፎካከሩ መደገፋቸውን መጀመሪያ የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ ሲሆን ሲቢኤስ ኒውስም በኋላ ላይ አረጋግጦታል።

አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት በምርጫ ክርክሩ ላይ ላሳዩት ደካማ አቋም በአማካሪዎቻቸው ከመጠን በላይ እንዲዘጋጁ በመደረጉ እንደሆነ ተነግረዋል። የጂል ባይደን ቅርብ ሰው ለሲቢኤስ እንደገለጹት ከሆነ ቡድኑን ከሚተቹት መካከል ጂል እንደሌሉበት ተናግረዋል።

የሁለቱም ዕጩዎች የዕድሜ ጉዳይ፣ የ81 ዓመቱ ባይደን እና የ78 ዓመቱ ትራምፕ ከሐሙሱ ክርክር በፊት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የባይደን ድክም ያለ ድምጽ እና ግልጽ ያልሆኑት መልሶች በዕጩነታቸው ላይ ያላቸውን ስጋት ያነሱ ሰዎች ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጭ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኒውዮርክ ታይምስ ርዕሰ አንቀጽ ቦርድ ባሰፈረው አስተያየት “[ባይደን] አሁን ሊያከናውኑት የሚችሉት ትልቁ ኃላፊነት በዳግም ምርጫው እንደማይወዳደሩ ማሳወቅ ነው” ብሏል።

ትራምፕም ቢሆኑ በምርጫ ክርክሩ ባሳዩት አቋም ከመተቸት አልተረፉም። የ2020 ምርጫ ተሰርቆብኛል ከሚለው ጀምሮ በርካታ ሐሰተኛ አስተያየቶችን ሰጥተዋል ተብሏል።

እሑድ ዕለት ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንቱን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።

ሴናተር ክሪስ ኩንስ "ስትወድቅ ትነሳ እና የበለጠ ትታገላለህ” ብለዋል።

የሜሪላንድ ኮንግረስ አባል ጄሚ ራስኪን በበኩላቸው በነሐሴ ወር በሚደረገው የዲሞክራሲያዊ ኮንቬንሽን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የሚሆኑት ባይደን ላይሆኑ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አንስተው ነበር።

“ዕጩውም እሳቸውም ሆኑ ሌላ ሰው በስብሰባው ላይ ዋና ተናጋሪ ይሆናሉ። ወደፊት ለመራመድ የምንሰበስበው በእሱ ዙሪያ ነው" ብለዋል

ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው ክርክሩ ለምን ትራምፕ ትክክለኛ ምርጫ እንደሆኑ ያሳያል ብለዋል።