ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ቀውስ- ኤምኤስኤፍ የሕክምና ባለሙያዎቼ በታጣቂዎች ድብደባ ደረሰባቸው አለ
ዓለም አቀፍ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ታጣቂዎች መኪኖቻቸውን ካስቆሙ በኋላ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸውን ገለፀ።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በመግለጫው ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው በካርቱም ደቡባዊ አቅጣጫ ወደሚገኘው የቱርክ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ ባለበት ወቅት ነው መሆኑን አስታውቋል።
ታጣቂዎች የሕክምና ባለሙያዎቹ ላይ ጥቃት ከማድረሳቸው በተጨማሪ አንድ መኪና መውሰዳቸውም ተመልክቷል።
በሚያዝያ አጋማሽ በሱዳን የጦር ጄነራሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በከተማው የደቡባዊ አቅጣጫ በኤምኤስኤፍ የሚደገፉ ሁለት ሆስፒታሎች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በጎ አድራጎት ድርጅቱ እያካሄደ ያለው የሰው ሕይወት የመታደግ ሥራ አደጋ ላይ መውደቁን አመልክቷል።
ባለፊት ሦስት ወራት በጦር ጄነራሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በከተማዋ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ሦስት ሚሊዮን ሱዳናውያን ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን አሁንም ግን ካርቱም ውስጥ በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ሕይወታቸውን ለማቆየት እየታገሉ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች አሉ።
እነዚህ ሱዳናውያን የሕክምና እርዳታ እና መድሃኒት ለማግኘት በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ባለሙያዎች በተለያየ ወቅት ገልፀዋል።
ኤምኤስ ኤፍ በሱዳን ከሚገኙ ጥቂት ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን በካርቱም እንዲሁም ኡምዱርማን የሕክምና ተቋማትን ይደግፋል።
ግጭቱ ከጀመረ ወዲህም 1ሺህ 600 ሕሙማንን በእነዚህ ከተሞች በሚገኙት ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና እርዳታ እንዲያኙ ማድረጉን ድርጅቱ ይናገራል።
ነገር ግን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በተደጋጋሚ ሠራተኞቹ ላይ ያነጣጠረ የፀጥታ እና የደህንንት ጥቃት እየበረከተ መምጣቱን ተከትሎ የሚሰጠውን ሰብዓዊ እርዳታ ሊያቆም አንደሚችል አስጠንቅቋል።
ሐሙስ እለት በደረሰው ጥቃት ወቅት ታጣቂዎች የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒት ጭነው የነበሩ አራት የኤምኤስ ኤፍ መኪኖችን በማስቆም በመኪናው ውስጥ ከነበሩ 18 ሰዎች ጋር እሰጥ አገባ መግጠማቸውን ተገልጿል።
ታጣቂዎቹ የቡድኑን አባላት ከማጥቃታቸውም ባሻገር ከሾፌሮቹ መካከል አንዱ ላይ የግድያ ዛቻ እንደሰነዘሩበት ተገልጿል።
“በድጋሜ እንዲህ ዓይነት ክስተት ከገጠመን፣ የመድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች አቅርቦታችን ከተደነቃቀፈ፣ እጅጉን እያዘንን በቱርክ ሆስፒታል ውስጥ የምንሰጠው አገልግሎት ይስተጓጎላል” ያሉት የድርጅቱ ኃላፊ ክርስቶፊ ጋርኒየር ናቸው።
ታጣቂዎች እና የግብረሰናይ ድርጅቱ ሰራተኞች እሰጥ አገባ የገጠሙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕሙማን ከሚገኙበት እና በቅርቡት በአየር ጥቃት የተጎዱ ሕሙማን ከሚታከሙበት ሆስፒታሉ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ስፍራ መሆኑ ተገልጿል።
“በየዕለቱ ሆስፒታሉ 15 በጦርነት የተጎዱ ሕሙማንን ይቀበላል፤ ሕይወት አድን ቀዶ ሕክምናዎችን ያደርጋል፤ እንዲሁም ለጽኑ ሕሙማኖች ሕይወት አድን ሕክምናዎችን ያቀርባል” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ አክለው ተናግረዋል።
እንደ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ ሆስፒታሉ የሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (ራፒድ ፎርስ/አርኤስኤፍ) አማፂያን በሚቆጣጠሩት ስፍራ ነው።
በካርቱም ሰላማዊ ዜጎች መኖርያ አካባቢዎች መሽገው የሚገኙ የሄሜድቲ ወታደሮችን ዒላማ በማድረግ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ይፈጸማል።
እስካሁን ድረስ በግጭቱ የሞቱ ሰዎች ይፋዊ አሃዝ 3000 የሚል ቢሆንም ቁጥሩ ግን ከዚህም ይልቃል የሚሉ ወገኖች አሉ።
አንዳንዶች በአገሪቱ ምዕራባዊ ክልል ዳርፉር ከፍተኛ ግጭት መካሄዱን ጠቅሰው በከተማዋ ብቻ የሟቾች ቁጥር 11 ሺህ ይሆናል ይላሉ።