የኢትዮጵያ ልዑክ ስለ ሕዳሴ ግድብ እና ቀይ ባሕር ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩ ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ወደ ዋሽንግተን ተጉዘው ከአሜሪካ ጋር "የመከላከያ ትብብር" የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የተፈራረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ፤ በአሜሪካ ቆይታቸው ስለ ሕዳሴ ግድብ እና ቀይ ባሕር መነጋገራቸው ተገለጸ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ትናንት ሰኞ ከዶ/ር ጌዲዮን ጋር በነበራቸው ውይይት፤ በመላው አፍሪካ ቀንድ የሚታዩ ግጭቶችን ስለመፍታት እና ስለማርገብ ተነጋግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአረብ እና አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ከተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ጋር ስለ "ቀይ ባሕር የማሪታይም ደኅንነት" ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ ጋር ይህ "ውጤታማ እና ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮች" ላይ ያተኮረው ንግግር የተደረገው አሜሪካ እና ኢትዮጵያ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት በፈጸሙበት ወቅት ነው።

የተፈረመው የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የአሜሪካ እና ኢትዮጵያን ግንኙነት "ለማጠናከር ያለመ" እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ኢትዮጵያን ሲወክሉ፤ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አሊሰን ሁከር ዋሽንግተንን ወክለው ፊርማቸውን አኑረዋል።

ሁለቱ አገራት በዚህ ስምምነት "ሁለትዮሽ ፣ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት" መስማማታቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ እንደሚጠቁመው ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መንግሥታዊ መዋቅሮች መካከል ምክክር እንዲካሄድ የሚያስችል ነው።

ምክክሩ "በየዓመቱ አንዴ አዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ዋሽንግተን" ውስጥ እንደሚካሄድ የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ "የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባውን በጋራ" እንደሚመሩትም አስረድቷል።

ምክክሩ ከሚደረግባቸው "ሦስት ምሶሶዎች" አንደኛው "የመከላከያ እና ጸጥታ ትብብር" ነው። ሁለቱ አገራት በዚህ ዙሪያ የሚያደርጉት ምከክር "የጸጥታ ጉዳይ ትብብርን ማጠናከር እና በጋራ የደኀንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተሳትፎን ማጠናከርን" እንደሚመለከት ተገልጿል።

"ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን" በሚመለከተው የምክክሩ ክፍል ደግሞ "የጋራ ጥቅምን እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምን እና ደኅንነትን የሚያስጠብቁ አካሄዶችን መፈተሽ እና በትብብር መሥራትን" እንደሚያካትት ተገልጿል።

በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ትስስር የበለጠ ማጠናከር እንዲሁም ኢንቨስትመንት እና ንግድን ማስፋትን የተመለከተ ምክክር የሚደረገው "የኢኮኖሚ ብልጽግና፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን" በሚይዘው ምሶሶ ነው ተብሏል።

ከዶ/ር ጌዲዮን ጋር የተገናኙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ኢትዮጵያ "በመላው ምሥራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት እና ውጥረቶችን በማርገብ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደምትጫወት" በአጽንኦት ማንሳታቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ስላላቸው "የደኅንነት አጋርነት" እንዲሁም በአገራቱ የሚገኙ "የንግድ ዕድሎች ለማሳደግ ስለተወሰዱ ጉልህ እርምጃዎችም" እንደተነጋገሩ ተገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ትናንት ሰኞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅትም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ደኅንነት ስላላት ሚና ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሩቢዮ "ስለ ቀጣናዊ መረጋጋት" እና "ጸረ ሽበር ትብብር" እንዲሁም "በአፍሪካ ቀንድ ለረዥም ጊዜ ደኅንነት መሠረት ስለመገንባት" ተነጋግረዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረብ እና አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ በኤክስ ገጻቸው ያወጡት ጽሑፍ እንደሚያሳየው ዋሽንግተን ከተገኘው ከኢትዮጵያ ልዑክ ጋር የሕዳሴ ግድብ እና ቀይ ባሕርንም በተመለከተም ውይይት ተደርጓል።

አማካሪው፤ "ስለ ናይል ወንዝ እና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገንቢ ውይይቶች አድርገናል" ብለዋል። "ቀጣናዊ መረጋጋትን" ስለማስፈን ባተኮረው ንግግራቸ ወቅት ደግሞ "የቀይ ባሕር ማሪታይም ደኅንነት" ጉዳይ ተነስቷል።

የእርስ በእስር ጦርነት ውስጥ ባለችው ሱዳን "ሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነትን ለማመቻቸት እና ዘላቂ ሰላም እንዲሳካ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን" በተመለከተ ሁለቱ አገራት ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ውይይት ዝርዝር አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር በነበረው ንግግር የቀይ ባሕር ጉዳይ የተነሳው አሜሪካ ከአዲስ አበባ ጋር ውጥረት ውስጥ ያለችው ኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማንሳት ማቀዷ በተዘገበ በቀናት ልዩነት ነው።

ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው የቀይ ባሕር መገኛ የሆነችው ኤርትራ ትኩረት ውስጥ የገባችው በኢራን ጦርነት የተነሳ ወሳኙ የባሕር መተለላፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ነው። የዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው አንድ ተንታኝ በበኩላቸው ይህ የአሜሪካ ዕቅድ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ የሚያደርግ መልዕክት እንደሚያስተላለፍ ጠቁመዋል።

ኤርትራ ባወጣችው መግለጫ አሜሪካ ማዕቀብ ልታነሳ ማቀዷን በበጎ እንደምትቀበለው የጠቆመችው ሲሆን "ይህ እርምጃ አገሪቱን በተመለከተ ሲተገበሩ የነበሩ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች በዘላቂነት እንዲታረሙ" ያደርጋል የሚል ተስፋዋን ገልጻለች።

በዋሽንግተኑ ውይይት የተነሳው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይም የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አንስቶት የነበረ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግድቡ ወደ ግብጽ የሚሄደውን የናይል ወንዝ "ፍሰትን ያስቆማል" እንዲሁም የተገነባው "በአሜሪካ ገንዘብ ነው" የሚል ንግግሮች በተደጋጋሚ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ጥር ላይ ደግሞ ለግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ በጻፉት እና ኢትዮጵያ በግልባጭ በተጠቀሰችበት ደብዳቤ፤ በናይል ወንዝ ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማደራደር ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ "ባለን የግል ወዳጅነት መንፈስ እና አሜሪካ ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ባላት ቁርጠኝነት፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን 'የናይል ውሃ መጋራት' ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት አደራዳሪነቷን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ ነኝ" ብለው ነበር።