ትራምፕ የኢራንን የሰላም ዕቅድ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለአሜሪካ የሰላም ዕቅድ የሰጠችውን ምላሽ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።
ቴህራን ምላሹን የሰጠችው በአደራዳሪዋ ፓኪስታን በኩል ሲሆን ግጭቱ ወዲያውኑ እንዲቆም እንዲሁም ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ጥቃት እንደማይፈጸምባት ማረጋገጫ እንዲሰጣት መጠየቋን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሰኞ ዕለት ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በእስያ ገበያ በበርሜል የ4.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 105.50 ዶላር ተሸጧል።
የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ከየካቲት የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ ዝግ ሀኗል።
ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል።
የዓለም አንድ አምስተኛው ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ በኋላ ቴህራን ለማቋረጥ የሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም በመግለጽ አስጠንቅቃለች።
ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት 21/ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ 26 የነዳጅ እና ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።
መርከቦቹ ላይ ጥቃት የደረሰው በተወንጫፊዎች፣ በአነስተኛ ጀልባዎች፣ በቦምብ ሲሆን አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከኦማን የባሕር ዳርቻ ወጣ ባለ ስፍራ እንዲሁም የዩኤኢ ፉጃይራህ ወደብ አቅራቢያ ነው።
ዓለም አቀፉ የባሕር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት በሆርሙዝ ወሽመጥ ከ1500 እስከ 2000 መርከቦች እንዲሁም 20 ሺህ ባህረተኞች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን አስታውቋል።
ዋና ዋና የኢነርጂ ኩባንያዎች የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ትርፋቸው መጨመሩን ይፋ አድርገዋል።
እሁድ ዕለት አራምኮ ባለፉት ሦስት ወራት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
ባለፈው ወር እንዲሁ ቢፒ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ትርፉ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የገለጸ ሲሆን ሼል ደግሞ ባለፈው ሳምንት ትርፉ ከፍ ማለቱን ተናግሯል።