የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ወደ አዲስ አበባ ሊያቀኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ካምፓላ እና አዲስ አበባን ሊጎበኙ ነው።
ማይክ ሐመር ቀድመው ወደ ካምፓላ በማቅናት በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ።
ዛሬ ሐሙስ ጥር 9/2016 በኡጋንዳ መዲና የሚካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ከያዛቸው ሁለት መወያያ ርዕሶች አንደኛው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አባል በሆኑበት በኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ “በጊዜ መጣበብ” ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች መሳተፍ እንደማይችሉ መግለጹ እየተነገረ ነው።
በአፍሪካ ቀንድ እና በአካባቢው የግጭት ስጋት ያስከተለው ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያ “ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው” በማለት ተቃውሞዋን አሰምታለች።
ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመስጠት በምላሹ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ለማግኘት ነው በመሪዎቻቸው ፊርማቸውን ያኖሩት።
ኢጋድ ይህን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ስብሰባ መጥራቱን ያወደሰችው አሜሪካ ተወካይዋ አምባሳደር ሐመር ምክክሩን እንዲታደሙ ልካለች።
የአሜሪካ አቋም፤ በአውሮፓውያኑ “1960 የድንበር ወሰን መሠረት አሜሪካ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ዕውቅና ትሰጣለች” የሚል ነው።
አምባሳደር ሐመር ከካምፓላ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ልዩ መልዕክተኛው በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ስላለው ግጭት ውይይት እንደሚያደርጉ ጠቁሟል።
አምባሳደሩ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉትን ግጭቶች አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰዎች እንዲጠበቁ እንዲሁም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥሪ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከአንድ ዓመት በፊት በስምምነት የተቋጨውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ የሚከናወነውን ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ተሃድሶ እና ማሰናበትን በተመለከተ እንዲሁም ተጎጂዎችን መሠረት ስላደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት ይወያያወሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያ ከደም አፋሳሹ የትግራይ እርስ በርስ ጦርነት መውጣቷን ተከትሎ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን፣ ከሶማሊለንድ ጋር በተደረሰው ስምምነት ምክንያት ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ተፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት ተከትሎ ቁጣዋን ስትገልጥ ቆይታለች።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ ረቡዕ ጥር 8/2016 ስብሰባ ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክረ ቤት ኦባሳንጆ ጣልቃ ገብተው ውይይት እንዲያስጀምሩ ጠይቋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የኅብረቱ ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በኢትዮጵያ እና በሱዳን ውስጥ ያሉ ግጭቶች መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
የስምምነቱ ይዘትና አከራካሪነት
የመግባቢያ ሰነዱ የግዴታ ተፈፃሚነት ያለው ሰነድ አይደለም። ነገር ግን ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማከራየት ዝግጁ እንደሆነች አስታውቃለች።
ስምምነቱ ወታደራዊ ትብብርንም ያቀፈ ነው። ሶማሊላንድ የባሕር በሯን ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ልታከራይ እንደሆነ ተናግራለች። ይህን አዲስ አበባም አረጋግጣለች።
በምላሹ ሶማሊላንድ ከአትራፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክሲዮን ልታገኝ እንደምትችል ተሰምቷል።
ነገር ግን ነገሮች የተወሳሰቡት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው። የቀድሞዋ የብሪታኒያ ግኝ ግዛት የነበረችው ሶማሊላንድ ነጻ አገርነቷን ካወጀች 30 ዓመት ቢያልፋትም ከየትኛውም አገር የሉዓላዊነት ዕውቅና ማግኘት አልቻለችም።
ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፣ ኢትዮጵያ ለአገራቸው ወደፊት ዕውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ እስካሁን አላረጋገጠችም። ባይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከስምምነቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ “ለሶማሊላንድን ዕውቅና መስጠትን በተመለከተ አቋም ለመያዝ” መስማማቱን ገልጧል።
ሶማሊላንድ ማለት ለሶማሊያ ግዛቷ አንድ ትልቅ አካል ናት። ሶማሊላንድ ከየትኛው አገር ጋር የምትገባው ስምምነት ያለሞቃዲሾ ይሁንታ መሆኑ ለሶማሊያ አደጋ ነው።
የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመ ማግስት ሶማሊያ ስምምቱን “የወረራ ድርጊት” ነው በማለት “ሰላም እና መረጋጋትን” ሊያናጋ እንደሚችል ጠቅሳ ነበር።
በስምምነቱ እጅግ የተቆጣችው ሶማሊያ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ እስከ መጥራት ደርሳለች።
ባለፈው ሰንበት የሶማሊያው ፕሬዘደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ “አገራችንን በምንችለው መንገድ እንመክታለን። የትኛውም ሊረዳን የሚችል አካል ካለ ለመተባበር ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ነፃ መውጣቷን ያወጀችው በአውሮፓውያኑ 1991 ነው። አገር መሆን የሚያስችላት ቁመና አላት። ማለትም የፖለቲካ ሥርዓት፣ መደበኛ ምርጫ፣ የፖሊስ ኃይል እና የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።
ባለፉት አሥርት ዓመታት ሶማሊያ በግጭት ስትናወጥ ሶማሊላንድ በአንጻራዊነት ሰላማዊ ጊዜ አሳልፋለች።
ነገር ግን የሶማሊላንድ አገር መሆን በየትኛውም ውጫዊ ወገን ዕውቅና አግኝቶ አያውቅም።
ሶማሊላንድ እንዳለችው ኢትዮጵያ ዕውቅና ብትሰጣት ይህ ውሳኔ በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረዋል።












