የቀድሞው የፖሊስ ኃላፊ ስለኢፕስቲን ባህሪ 'ሁሉም እንደሚያውቅ' ትራምፕ ከ20 ዓመት በፊት ነግረውኛል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የፍሎሪዳ ፖሊስ አዛዥ በአውሮፓውያኑ 2006 ከዶናልድ ትራምፕ የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው እና "ሁሉም ሰው" የጄፍሪ ኤፕስቲንን ባህሪ እንደሚያውቅ እንደነገሯቸው የፍትህ ቢሮ ያወጣው የኤፍቢአይ ሰነድ አመለከተ።
ሰነዱ እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ከቀድሞው የፓልም ቢች የፖሊስ አዛዥ ጋር ኤፍቢአይ ያደረገው ቃለ ምልልስን የያዘ ነው።
የፖሊስ አዛዡ ትራምፕ መምሪያው በኤፕስቲን ላይ ምርመራ ከጀመረ በኋላ ደውለው "እሱን በማስቆምክ ፈጣሪ ይመስገን፤ ይህን ሲያደርግ ሁሉም ያውቃል" ማለታቸውን ተናግረዋል።
የፖሊስ አዛዡ ስም ከሰነዱ ላይ የተሰረዘ ቢሆንም ቃለ መጠይቁ የተካሄደው በወቅቱ የፓልም ቢች የፖሊስ አዛዥ ከነበሩት ጋር መሆኑን ይገልጻል።
ስለዚህ በወቅቱ ትራምፕ የደወሉላቸው የፖሊስ አዛዥ ማይክል ሬይተር መሆናቸው ታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ከየወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ጥፋት አለመፈጸማቸውን በተደጋጋሚ የገለፁ ሲሆን ስለወንጀሎቹም እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ተደረገ የተባለው የስልክ ጥሪ ትራምፕ ምን እና ከመቼ ጀምሮ እንደሚያውቁ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል።
ኢፕስቲን በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር በዋለበት በ2019 ትራምፕ ስለወሲብ ወንጀለኛው "ጥርጣሬ" ይኖራቸው እንደሆን ጋዜጠኞች ሲጠይቋቸው "አይ፣ ምንም አላውቅም ነበር። ምንም አላውቅም ነበር። ከእሱ ጋር ከተነጋገርን ረዥም ዓመታት አልፈዋል" ብለዋል።
በቅርቡ ይፋ ከተደረጉት የኢፕስቲን ዶሴዎች መካከል የተገኘው ይህ የኤፍቢአይ ሰነድ ሬይተር እአአ በ2006 ሐምሌ ወር ላይ ትራምፕ ከማር-አ-ላጎ ክለባቸው ኢፕስቴንን ማስወጣታቸውን እና "በኒውዮርክ ያሉ ሰዎች አስጸያፊ መሆኑን ያውቃሉ" እንዳሏቸው ተናግረዋል።
ሬይተር በተጨማሪም ጊስሌይን ማክስዌልንም በሚመለከት እንደነገሯቸው ገልጸው የኢፕስቲን "አንቀሳቃሽ" እንደነበረች እና "ክፉ ናት፤ እርሷ ላይም አተኩሩ" ማለታቸው በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ማክስዌል እአአ በ2021 ለኢፕስቲን ታዳጊዎችን በመመልመል ወንጀል ተፈርዶባታል።
ሬይተር ለኤፍቢአይ ትራምፕ ኢፕስቲን ከታዳጊ ሴቶች ጋር እያለ እዚያ እንደነበሩ እና "በፍጥነት ለቅቀው መውጣታቸውን" እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
እንደ ሰነዱ ከሆነ ትራምፕ በኢፕስቲን ላይ ምርመራ መጀመሩን ሲሰሙ ወደ ፍሎሪዳ ፖሊስ "መጀመሪያ ከደወሉ ሰዎች መካከል አንዱ" መሆናቸው ተገልጿል።
እአአ በ2006 ፓልም ቢች ፖሊስ ወንጀለኛውን ኢፕስቴን ታዳጊዎችን ለወሲብ ተግባር ይመለምላል በሚል በቀረበበት ክስ ላይ ምርመራ ጀምሮ ነበር።
በኃላ ላይ ጉዳዩ ወደ ፌደራል አቃቤ ሕጎች የተመራ ሲሆን በ2008 ኢፕስቲን አወዛጋቢ ስምምነት አድርጓል።
ይህም ጠንከር ያሉ ክሶች እንዳይቀርብበት እና ያለ መከሰስ ስምምነት ላይ እንዲደርስ አስችሎት ነበር።
የፍትህ ቢሮ ለቢቢሲ በሰጠው መረጃ መሠረት "ፕሬዚዳንቱ ከ20 ዓመት በፊት የሕግ አስከባሪ አካላትን ማናገራቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ አላገኘንም" ብሏል።
ማክሰኞ ዕለት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮላይን ሌቪት ስለ ስልክ ጥሪው ተጠይቃ "በ2006 ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ አልሆነም ይሆናል። መልሱን አላውቀውም"
"ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሁሌም የሚሉት ከ ማር- አ- ላጎ ክለባቸው ኢፕስቲንን እንዳስወጡት ነው፤ ምክንያቱም ጄፈሪ ኢፕስቲን ተንኮለኛ ስለነበር ነው" ብላለች።
"በዚህ ስልክ ልውውጥ ላይም ያ እውነት መሆኑ ነው የሚታየው። እውነት ሆኖ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሉትን የሚያጠናክር ነው"
ቢቢሲ ሬይተርን ለማገኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ትራምፕ እና ኤፕስቲን በ1990ዎቹ ወዳጅ በነበሩበት ወቅት አብረው የተነሷቸው ፎቶግራፎች ይታያሉ።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ እና ዋይት ሐውስ በ2004 አካባቢ ከእሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማቋረጣቸው በፊት ስለ ኤፕስታይን ወንጀሎች ምንም እውቀት እንዳልነበራቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ትራምፕ እንደተናገሩት አለመግባባታቸው የተከሰተው ኤፕስታይን ሠራተኞቹን ከማር-አ-ላጎ "ለመውሰድ" ሲሞክር እንደነበር ካወቁ በኋላ ነው።















