በስዊዲን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ በተፈጠረ ያልታወቀ ሽታ 8 ሰዎች ሆስፒታል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በስዊዲን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ባጋጠመ ያልተለመደ ዓይነት ሽታ ምክንያት ስምንት ሰዎች ሆስፒታል ሲገቡ ሠራተኞቹ ሕንጻውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተነገረ።
ከዋና ከተማዋ ስቶክሆል ወጣ ብሎ በሚገኘው የአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ አርብ ዕለት የተፈጠረውን ምንነቱ ያልታወቀ ጠረንን ተከትሎ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሆስፒታል ገብተዋል።
ያልተለመደ ዓይነት ሽታ በመሥሪያ ቤቱ መከሰቱን ሠራተኞች ማሳወቃቸውን ተከትሎም ለደኅንነት ሲባል 500 የሚደርሱ ሰዎች ህንጻውን ለቀው እንዲወጣ ተደርጓል።
መጀመሪያ ላይ በህንጻው ውስጥ የተከሰተው ሽታ ካፈተለከ ጋዝ የተፈጠረው ነው የሚል ጥርጣሬ የነበረ ቢሆንም፣ የደኅንንት ሠራተኞች በህንጻው ውስጥ እና ከውጪ ምንም ዓይነት የጋዝ ምንጭ ማግኘት አልቻሉም።
ፖሊስ በበኩሉም በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የተፈጠረውን ጠረን ምንጭ ለማወቅ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እያካሄደ ነው።
የሲዊዲን መገናኛ ብዙኃን በህንጻው ጣራ ላይ የሚገኙ የሽታ መለያ መሳሪያዎች ፎስጂን የተባለ ጋዝ መለየታቸውን ቢዘግቡም ባለሥልጣናት ግን ይህንን አላረጋገጡም።
ፎስጂን የተባለው ኬሚካል ፕላስቲክ እና ፀረ ተባዮችን ለመሥራት የሚውል ሲሆን፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ለበርካታ ሰዎች በኬሚካል መሞት ምክንያት ነው ይባላል።
በስዊዲን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ባለፈው አርብ አደገኛ የሆነ ኬሚካል ሽታ መፈጠሩ ሪፖርት የተደረገው እኩለ ቀን ላይ ነበረ። ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተቋም ጥሪ ከተደረገለት በኋላ ጉዳት እንዳይደርስ ተሰማርቷል።
ከማዕከላዊው ስቶክሆልም ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ባለው የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ላይ ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ ሠራተኞች እንዲወጡ እና ከህንጻው በዙሪያ እንቅስቃሴ የተከለከለ ሲሆን፣ በአቅራቢያው ያለ መንገድም እንዲዘጋ ተደርጓል።
ሽታው ተከስቷል መባሉን ተከትሎ የመተንፈስ ችግር የገጠማቸው ስድስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ሆስፒታል ሄደዋል። ከእነዚህም መካከል “በስፍራው ሲደርሱ ጠረኑን ያሸተቱ” የፖሊስ መኮንኖች ይገኙበታል።
ከስፍራው የወጡ ምሥሎች ፖሊስ መኮንኖች የጋዝ መከላከያ ጭምብል አጥልቀው እንዲሁም ሄሊኮፕተር በአካባቢው ሲንዣብብ አሳይተዋል።
ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በአቅራቢያ በሚገኙ ህንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ለደኅንነታቸው ሲባል መስኮታቸውን እንዲዘጉ ተነግሯቸዋል።
አንድ በአካባቢው የሚገኙ መምህር ደግሞ ተማሪዎች በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን ለአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። በኬሚካል ስጋት ምክንያት ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን በተደረገው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወደ ቤታቸው ለመግባት አልተፈቀደላቸውም።
ይህ ሁኔታ የተከሰተው የስዊዲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ለጉብኝት ወደ ሃንጋሪ በተጓዙበት ወቅት ነው። ሃንጋሪ ስዊዲን የኔቶ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ያላጸደቀች ብቸኛዋ የኔቶ አባል አገር ስትሆን፣ የአገሪቱ ፓርላማ ሰኞ የስዊዲንን ጥያቄ ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።












