በሱዳን የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካምፕ ሦስት ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸው ተገለጸ

የቱናይድባህ ካምፕ

የፎቶው ባለመብት, SM

በሱዳን የኢትዮጵያ የስደተኞች የመጠለያ ካምፕ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ተከስቶ ሦስት ስደተኞች መያዛቸውን የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም አስታወቀ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በምሥራቅ ሱዳን በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ በሽታው መከሰቱን አመልክቶ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባሉበት ቱናይድባህ ካምፕ ውስጥ ሦስት ስደተኞች በበሽታው ታመዋል ብሏል።

በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የሚገኘው የቱናይድባህ ካምፕ በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ማስጠለሉ ይነገራል።

በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሰረት ካምፑ ወደ 23,000 የሚጠጉ ስደተኞችን ይዟል።

በስደተኛ ካምፖቹ በሽታው መከሰቱን እንዳሳሰበው ለቢቢሲ የገለጸው ተቋሙ፣ በከሳላ ግዛት በሚገኘውና ሸገራብ የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ ውስጥም በሽታው ተከስቶ አንድ ሰው መታመሙን ገልጿል። 

በበሽታው የተጠቁ ስደተኞችም በጤና ማዕከላት ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ በበሽታው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ደግሞ ተለይተው አስፈላጊውን እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተቋሙ አመልክቷል።

በዚህም የሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች አጋሮች የስደተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ወረርሽኙ የበለጠ እንዳይዛመት ለመከላከል ፈጣን ምላሽ እየሰጡ ነው ተብሏል።

ተቋማቱ በሽታው በተከሰተባቸው ካምፖች ከጤና ባለሙያዎች ጋር የምርመራ እና የጋራ ክትትሎችን በማድረግ ወረርሽኙ የበለጠ እንዳይዛመት ለመግታት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። 

በበሽታው የተያዙ ህመምተኞችን እንክብካቤ ከመስጠት በተጨማሪ የታመሙ ሰዎች የቤተሰበ አባላትም ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

ተቋማቱ በጥምረት ለስደተኞቹ እና ለአካባቢው ማኅበረሰቦች የጤና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ሳሙና እና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ መገልገያዎች ለስደተኞች እየተከፋፈሉ ነው ተብሏል።

ተጨማሪ ስደተኞች በበሽታው እንዳይያዙ ለመከላከል የሚወሰዱ ማናቸውም የመከላከያ እርምጃዎች ከዓለም የጤና ድርጅት የዝንጆሮ ፈንጣጣ መመሪያ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ እና የስደተኞችን ደኅንነት መረጋጋጥም እንዳለበት ዩኤኤችሲአር አሳስቧል። 

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት እዚህም እዚያም ማበጥ እና በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል።

ሙቀቱ ጋብ ሲል ሰውነት ከፊት ጀምሮ ማሳከክ ይጀምራል። መላው ሰውነትን ቢያሳክክም ክንድና እግር የበለጠ ያሳክካሉ።

የሚከሰተው እከክ በጣም የሚያምና በተለያየ ደረጃ የሚያልፍ ነው።

ቆዳ ላይ የሚከሰተው እብጠት ኋላ ላይ ቆዳ እንዲቆስልና እንዲረግፍም ያደርል። ጠባሳ ጥሎም ሊያልፍ ይችላል።

ሕመሙ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ሲሆን ከ14 እስከ 21 ቀናት ይወስድበታል።

በሽታው እንዴት ይይዛል?

በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ተጋላጭ ናቸው። 

በቆዳችን ክፍተቶች በኩል፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ቫይረሱ ወደ ሰውነታች ይገባል።

በወሲብ ወቅት ባለ ንክኪም ቫይረሱ ይተላለፋል።

በቫይረሱ ከተያዙ ዝንጀሮዎች፣ አይጦች ወይም ሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ ከተደረገ ቫይረሱ ወደ ሰው ይተላለፋል።

ቫይረሱ በልብስ ወይም በሌሎችም ንክኪ ባላቸው ጨርቆች በኩልም ይተላለፋል።

አብዛኞቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ለከፋ ሕመም አይዳረጉም።

ልክ እንደ ፈንጣጣ በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ይጠፋል። ሆኖም ግን በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስም ይችላል።