የሴኔጋሉ ፕሬዚደንት በመጋቢት ወር መጨረሻ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተስማሙ

ፕሬዚደንቱ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዚደንት ሳል ሐሙስ ምሽት የሰጡትን የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ለማየት በመላ አገሪቷ በርካቶች ተሰባስበው ነበር።

የሴኔጋሉ ፕሬዚደንት ማኪ ሳል የሥልጣን ጊዜያቸው መጋቢት 24/ 2016 ዓ.ም ሲያበቃ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ።

ሆኖም ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ባለመቆረጡ በአገሪቷ ውስጥ ውጥረት ተከስቷል።

ፕሬዚደንቱ እሑድ ዕለት ይካሄዳል ተብሎ ታቅዶ የነበረውን የምርጫ ጊዜ ወደ መጪው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ማራዘማቸው የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ አስከትሏል።

ሳል በቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ ምልልሳቸው ላይ የምርጫው ቀን በመጪው ሰኞ በሚካሄደው “ፖለቲካዊ ውይይት” እንደሚወሰን ተናግረዋል።

ሆኖም ተቃዋሚዎች በንግግሩ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆኑም። ይህም ውጥረቱን ያረግባል ተብሎ የተጣለውን ተስፋ አጨልሞታል።

ከ19ኙ ፕሬዚደንታዊ እጩዎች መካከል 16ቱ፣ ፕሬዚደንቱ “ብሔራዊ ምክክር” ሲሉ በጠሩት ውይይት ላይ እንደማይሳተፉ የገለጹ ሲሆን በርካታ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በናይጄሪያ፣ አቡጃ ለሚካሄደው የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ስብሰባ ያቀኑት ሳል፣ ባለፈው ሳምንት የሰኔጋል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫውን ማራዘም ሕገ ወጥ ነው ካለ በኋላ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን እንዲቆርጡ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።

ፕሬዚደንቱ ቀደም ብሎ የምርጫውን ጊዜ ለማራዘም ያሳለፉት ውሳኔም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

በርካቶች የምርጫው ጊዜ መራዘሙ በመፈንቅለ መንግሥት እና በወታደራዊ መንግሥታት በሚናጠው ቀጠና ፕሬዚደንት ሳል ላልተወሰነ ጊዜ መሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ሳል ሐሙስ ምሽት በቴሌቪዥን ባስተላለፉት ንግግር፣ እርሳቸው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ሥልጣናቸውን እስከሚለቁ የሚተካቸውን ሰው ለመምረጥ በቂ ጊዜ የለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም ምን መሆን እንዳለበት ምክክሩ ይወስናል ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው ታዋቂውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኦስማን ሶንኮን ከእስር ለመፍታት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ሶንኮ ለክስ እና ለእስር የተዳረገው በቀጣዩ ምርጫ ተገዳዳሪ በመሆን ለገዢው ፓርቲ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ይከሳሉ።

የፖለቲከኛው እስር ባለፈው ዓመት በመላ አገሪቷ ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር።

የሴኔጋል የሕገ መንግሥት ምክር ቤት የምርጫ ጊዜውን ማራዘም ሕገ ወጥ ነው ካላ በኋላ በርካታ የፕሬዚደንቱ ተቃዋሚዎች ከእስር ተለቀዋል።

ሆኖም ፕሬዚደንቱ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ባለመቁረጣቸው በስልጣን ለመቆየት የሚያደርጉት ስልት ነው በሚል በተቺዎቻቸው ዘንድ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

ፕሬዚደንት ሳል ለሁለት የሥልጣን ዘመን አገሪቷን የመሩ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚደንት ሆነው ሲመረጡ ከተሰጣቸው ጊዜ በላይ በሥልጣን መቆየት እንደማይፈልጉ ቃል ገብተው ነበር።