ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን ወደ ሥልጣን ያመጡት አማካሪ

“ጠላት ሊኖራችሁ ይገባል” ይላሉ ጆርጅ ቢርንባም።

ግለሰቡ ‘ሞደርን ፖፒሊዝም’ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ አባት እንደሆኑ ይነገራል።

‘ዘመናዊ ፖፒሊዝም’ን በግርድፉ ስናየው በተራው ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍን ማዕከል ያደረገ ነው።

ወይም የተራውን ሰው ስስ ልብ በመንካት ላይ ያተኮረ ነው።

እሳቸው እንደሚሉት “በሁሉም ዘንድ የሚወደድ ሰው ማግኘት ከባድ ነው። በጣም ጥቂቶች ናቸው ይህንን ማግኘት የቻሉት።”

ጆርጅ ቢርንባም ለ30 ዓመታት በፖለቲካ አማካሪነት ሰርተዋል።

በዚህም ዘመናቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ አድርገዋል።

በተጨማሪ ከሃንጋሪው መሪ ቪክተር ኦርባን ሥልጣን መቆናጠጥ ጀርባም አሉ።

በብዙ አገራት የሚያማክሯቸው ፖለቲከኛ ደንበኞች አሏቸው።

በርካታ ጊዜያቸውንም በበረራ ከማሳለፋቸው አንጻር ‘ኑሯቸው በሰማይ ላይ ነው’ ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ሆኖም ኒውዮርክ፣ ዱባይ እና ሃራሬ በርካታ ጊዜ የሚያዘወትሯቸው ከተሞች ናቸው።

ጆርጅ ቢርንባን ከ‘አርተር ልጆች’ አንዱ በመሆን ነው ስማቸውን የገነቡት።

አርተር ማን ነው? ያላችሁ እንደሆነ፤ በአሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ዘመቻ ጥበብን ስላራቀቁት አርተር ፊንክልስቴይን ነው የምናወራው።

አርተር በአውሮፓውያኑ 1972 በአሜሪካ ወደ መሪነት የመጡትን ሪቻርድ ኒክሰንን ጨምሮ በርካታ ሪፐብሊካን መሪዎች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ያገዙ የሂሳብ ሊቅ ናቸው።

አርተር ለጆርጅ ቢርባን የፖለቲካ ሕይወት ፈር የቀደዱ ናቸው። በአንድ ወቅትም የንግድ አጋር ነበሩ።

“አንድ ፖለቲከኛ ምርጫው ወደ አንተ እንዲያዘነብል ለማድረግ በጽንፍ ስፍራ የሚያስቀምጡ እንደ አደንዛዥ ዕጽ፣ ወንጀል፣ ዘርን የመሳሰሉ ጉዳዮች ለማንሳት መሞከር አለብህ” ሲሉም አርተር በአውሮፓውያኑ 1970 ማስታወሻቸው ላይ ጽፈዋል።

ሆኖም ይላሉ አርተር “ተፎካካሪዎችህ እነዚህን ጽንፍ የሚያስይዙ ጉዳዮችን ካነሱ፤ ያን ጊዜ ችግር ላይ ነህ” በማለትም አስፍረዋል።

ጆርጅ ቢርንባም የቤንያሚን ኔታንያሁ አማካሪ ሲሆኑም፣ አርተር አጠገባቸው ነበሩ።

ሁለቱ አማካሪዎች ድንቅ በተባለ ስኬት ኔታንያሁ በአውሮፓውያኑ 1996 ወደ ሥልጣን እንዲመጡ አስችለዋል።

ወቅቱም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን ከተገደሉ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትም ሺሞን ፔሬዝ ነበሩ።

ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚደረገው ድርድር “ፔሬዝ ኢየሩሳሌምን ለሁለት ሊከፍሏት ነው” የሚሉ መፈክሮችም ተሰሙ። ይህም መፈክር ነው የመራጮች ልብ ውስጥ የቀረው። ከዚህ መፈክር ጀርባም ጆርጅ ቢርንባም አሉበት።

መፈክሩ እውነት ነበር? ፔሬዝ ኢየሩሳሌምን ለሁለት ሊከፍሉ ነበር? ለጆርጅ ቢርንባም ቢቢሲ ያቀረበለት ጥያቄ ነበር።

“ኢየሩሳሌምን ለሁለት ትከፈለላች የሚለው እውነት አይመስለኝም” ብለዋል አሁን ሲመልሱ ጆርጅ ቢርባን

“ነገር ግን የተወሰኑ የማዘጋጃ ቤት አካባቢዎች ነበሩ። የሰላም ስምምነቱ አካል ተደርገው ለፍልስጥኤም አስተዳደር እንዲሰጡ ውይይት ተደርጎባቸዋል” ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2008 ጆርጅ ቢርባን ለሃንጋሪው ፖለቲከኛ ቪክቶር ኦርባን መሥራት ጀመሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ የቀኝ ክንፍ አክራሪ የሆነው 'ፌዴዝ' የተሰኘው ፓርቲያቸው ከፍተኛ ድልን ተጎናጸፈ።

ቪክቶር በመሪነት ሥልጣን ላይ ወጡ። ሦስት ዓመት በመሪነት ከተቀመጡ በኋላም ለመጪው ምርጫ መዘጋጀት አስፈላጊ ነበር። ይህንንም ለማድረግ ለቪክቶር አዲስ ጠላት አስፈለጋቸው። ተወሰነ። ሃንጋሪያውያን በሙሉ ሊፈሩት የሚገባ ሰው ተዘጋጀ።

ከበርካታ አስተያየቶች እና የዳሰሳ ጥናቶች በኋላ ኢላማ የሚደረገው ሰው ተገኘ። ጆርጅ እና አርተር የ85 ዓመቱ የሃንጋሪ ተወላጅ የሆኑት አሜሪካዊው ቢሊየነር እና በጎ አድራጊ ጆርጅ ሶሮስን መረጡ።

ቪክቶር ኦርባን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጆርጅ ሶሮስን የሕዝብ ጠላት አድርገው በመሳል “ጥንብ እርኩሳቸውን” እያወጡ ሰድበዋቸዋል።

“ጆርጅ ሶሮስን ኢላማ ማድረጉ በጣም ጥሩ ነበር” ይላሉ ጆርጅ ቢርንባም

“ምክንያቱም በሃንጋሪ በርካታ ሰዎች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ፖለቲካውን የሚያሾሩትን ቢሊየነር ሃሳብ አልወደዱትም። ጆርጅ ሶሮስ ፖለቲካውን እና ፖሊሲዎችን ይቆጣጠሩ ነበር።”

ነገር ግን እውነት ጆርጅ ሶሮስ ፖለቲካውን እና ፖሊሲውን በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር?

በአውሮፓውያኑ 2015 ጆርጅ ቢርንባም ለቪክቶር ኦርባን መሥራት አቆሙ። በዚያው ዓመትም የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ ጠላት አገኙ - ሙስሊም ስደተኞች።

በዚያው ዓመትም ጆርጅ ሶሮስ የአውሮፓ ኅብረት በርካታ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን እንዲቀበል ሃሳብ አቀረቡ። የሃንጋሪው መሪም “የሶሮስ ዕቅድ” ያሉትን ለመተቸት ወደኋላ አላሉም።

አይሁዳዊው በጎ አድራጊ ሶሮስ፣ ክርስቲያን አውሮፓን በሙስሊም ስደተኞች ለማጥፋት በማሴር ተከሰሱ።

ይህ ሃሳብ ቀድሞውኑም በአውሮፓ ቀኝ አክራሪ ጽንፈኞች ደግሞ “የመዋጥ እና የመተካት ጽንሰ ሃሳብ” በሚልም ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ነበር።

ስደተኞች በሃንጋሪ ተፈሩ። ከዓመታት በፊት ይውጧችኋል፣ ሊያጠፏችሁ ነው የተባሉትን አይሁዶችን እና ጂፕሲዎችን ስደተኞች ተኩ። ጆርጅ ሶሮስን የሚቃወሙ ሰልፎች ከሃንጋሪ ተነስቶ በዓለም ተስፋፋ።

“ጠላቶቻችንን በስማቸው ለመጥራት አትፍሩ። እነሱ ምህረት አያውቁም። ለአፍታም ጆርጆ ሶሮስን አስቡት” ሲሉም ቪክቶር ኦርባን በአሜሪካ ቴክሳስ ባለፈው ዓመት በነበረው በወግ አጥባቂዎች ጉባዔ ለሪፐብሊካን ፖለቲከኞች ተናገሩ።

“ጆርጅ ሶሮስን በደንብ አውቀዋለሁ። እሱ ተቃዋሚዬ ነው። በምንሰራቸው ነገሮች ምንም አያምንም” ሲሉም የሃንጋሪው መሪ ለአሜሪካ ጋባዦቻቸው ተናገሩ።

የጆርጅ ቢርንባም ባለቤት ዩክሬናዊት ናት። ጥንዶቹ ዩክሬንን አዘውትረው ይጎበኛሉ።

የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮም የቅርብ ጓደኛቸው ናቸው።

ቢርንባም ስለ ፑቲን የሚሉት አላቸው። ባለፈው ዓመት ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን የላኩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሊበራሊዝም ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ይናገራሉ።

የሩሲያው መሪ ሊበራል የሆነውን የምዕራቡን ዓለም የመድብለ ባህላዊነት፣ የስደት ፖሊሲ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶችን እያነሱ መቆርቆዛቸውን ዕድል ባገኙ ቁጥር ያነሳሉ ይላሉ።

ዩክሬን ለመቀላቀል እየሞከረች ያለውም ምዕራቡ ዓለም ገጽታ ይህ አይደለምን? ይህስ የሊበራል ዓለም አይደለም እንዴ ጆርጅ ሶሮስ የሚቀበሉት?

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት “ነጻነት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ የዲሞክራሲ መሠረታዊነት አስታውሶናል” ይላሉ ጆርጅ ቢርንባም።

ጆርጅ ሶሮስን መንገድ ላይ ቢያገኟቸው መጠጥ እንደሚጋብዟቸው ጆርጅ ቢርንባም ይናገራሉ።

“በብዙ ነገሮች ላይ አንስማማም። ነገር ግን የምዕራቡ ዓለም ዲሞክራሲ፣ ሊበራል ዲሞክራሲ መጻዒ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ተመሳሳይ እሳቤዎች ካለን ለማወቅ እፈልጋለሁ” ሲሉም አስረድተዋል።

“በሁለቱም በኩል ጽንፍ ላይ የተቀመጡ እሳቤዎች ላይ ችግር አለብኝ። የግራ ዘመም ተራማጆችም ሆኑ የቀኝ አክራሪ ጽንፈኞች ጫፍ ላይ ያለ ነገርን አልቀበልም” ይላሉ።

የሃንጋሪው መሪ ቪክቶር ኦርባንን በተመለከተ ለመጨረሻ ጊዜ ከተነጋገሩ አስር ዓመት ገደማ እንዳለፋቸው፣ በተዋዋቁበትም ወቅት ያደንቋቸው እንደነበር ይናገራሉ።

“የተማሩ፣ ስለ ምጣኔ ሃብት ጥልቅ እውቀት ያላቸው፣ ፖሊሲዎችን በደንብ የሚረዱ ነበሩ። ይህ ብዙም የተለመደ አይደለም” ይላሉ ስለ ሃንጋሪው መሪ ሲናገሩ።

ሆኖም ቪክቶር ኦርባን በሥልጣን ላይ ለረጅም ዓመት እንደቆዩ ያምናሉ።

በአውሮፓውያኑ 2015 የሃንጋሪው መሪ “እያንዳንዱ ስደተኛ አሸባሪ ሊሆን ይችላል” የሚል አስተያየት ሰጡ።

ባለፈው ዓመትም መሪው ለደጋፊዎቻቸው “እርስ በእርስ ለመዋለድ እና ለመቀላቀል ፈቃደኞች ነን። ነገር ግን ከሌላ ዘር ጋር የተቀላቀለ ድብልቅ ዘር ሕዝቦች መሆን አንፈልግም” አሉ።

ጆርጅ ቢርንባም የሃንጋሪውን መሪ ሁለቱን አስተያየቶች በጥብቅ ይቃወማሉ።

ሆኖም የጆርጅ ቢርንባም ተቺዎች በፖለቲካ ውስጥ ጽንፍ ላይ መቆምን ከፍተኛ ስፍራ ያደረሱ ናቸው ሲሉ ይተቿቸዋል።

እሳቸውስ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ።

“ምርጥ መሪዎች የጋራ ግቦቻችንን የሚያስታውሱ እንጂ ልዩነቶቻችን የሚያጎሉ አይደሉም። ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን የሰዎች ተስፋ እና ህልሞች እውን መሆናቸውን ማረጋገጥ ቅድሚያ መሰጠት አለበት” ይላሉ።