የኦባማ ቤተሰብ ምግብ አብሳይ ተፈሪ በአደጋ አረፈ

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቤተሰብ የግል ምግብ አብሳይ (ሼፍ) የሆነው ተፈሪ ካምፔል በአደጋ ህይወቱን አጣ።

ተፈሪ ህይወቱን ያጣው ‘ፓድል ቦርዲንግ’ በተሰኘ በውሃ ላይ የመቅዘፍ የስፖርት እንቅስቃሴ በኦባማ የማሳቹሴት መኖሪያ ቤት አካባቢ በደረሰበት አደጋ ነው።

የ45 አመቱ ተፈሪ ካምቤል ፕሬዚዳንት ኦባማ በስልጣን ላይ እያሉ በዋይት ሃውስ እንዲሁም ከለቀቁበት ከጎሮጎሳውያኑ 2016 ጀምሮ በቤታቸው በምግብ አብሳይነት እየሰራም ነበር።

እሁድ እለት ማርታ ቫይንያርድ በተሰኘው ስፍራ በሚገኘው የኤድጋርታውን ግሬት ፖንድ ሃይቅ ላይ መጥፋቱ ተሰምቷል።

የኦባማ ቤተሰብ ተፈሪ በማዕድ ውስጥ የነበረውን ችሎታ እንዲሁም ሰብዓዊነቱን የሚያደንቅ መግለጫ አውጥተዋል።

“ተፈሪ አንድ ተወዳጅ የቤተሰባችን አባል ነበር። በዋይት ሃውስጥ በነበረው ቆይታም ሆነ በቤታችን ለምግብ አሰራር የነበረው ፈጠራ የታከለበት ሙያና የነበረው ፍቅር እንዲሁም ሰዎችን የማሰባሰብ ችሎታ በጣም የሚያስደንቅ ነበር” ሲሉም ባራክ ኦባማና የቀድሞዋ ቀዳማዊት ሚሼል አባማ ሰኞ እለት ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።

“በዓመታት ውስጥ ውስጥ ምን ያህል በጣም ደግ፣ ተጫዋችና የሚያዝናና ሰው መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ህይወታችንንም ብሩህ አድርጎታል” ብለዋል።

ተፈሪ በወቅቱ አደጋ በደረሰበት ወቅት የኦባማ ቤተሰቦች ቤት እንዳልነበሩም ፖሊስ አስታውቋል።

እሁድ እለት ውሃ ውስጥ የገባ እየቀዘፈ የነበረ ግለሰብ በውሃው ላይ ለመንሳፈፍ ሲታገል ትንሽ ከቆየ በኋላ እንደሰመጠና ከዚያ በኋላ አልታየም የሚል የፖሊስ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎም ፍለጋዎች ተጧጡፈው ነበር።

ሌላ ቀዛፊ በወቅቱ ውሃ ውስጥ አብሮት የነበረ ሲሆን በውሃው ውስጥ ሲሰምጥ እንደተመለከተው አክሏል።

ሰኞ ዕለት አስከሬኑ በግምት ከኃይቅ ዳርቻው በ30 ሜትር ጥልቀት ውስጥ መገኘቱም ተነግሯል።

የማሳቹሴትስ ፖሊስ የተፈሪን ሞት በማጣራት ላይ ቢሆንም አደጋ ነው ተብሎ እንደሚታመንም ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።