በቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሴረው ኦስትሪያዊ የሽብር ክስ ተመሰረተበት

የፎቶው ባለመብት, PA
አንድ ኦስትሪያዊ በነሐሴ 2024 በቪየና በተካሄደው የቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በማሴር በሽብርተኝነት እና በሌሎች ወንጀሎች ክስ ተመሰረተበት።
አቃቤ ሕግ እንደገለጸው የ21 ዓመቱ ተጠርጣሪ ቤራን ኤ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የሽብርተኛ ድርጅት አባል በመሆን፣ ፈንጂዎችን በመስራት እና በሕገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ለመግዛት በመሞከር ተከሷል።
እንዲሁም ለኢስላሚክ ስቴት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጭ እንደነበር ተገልጿል። ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው የቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ከመጀመሩ በፊት ከሲአይኤ በተገኘ ትቆማ መሠረት ነው።
አሜሪካዊቷ ቴይለር ስዊፍት በቪየና ኤርነስት ሃፔል ስታዲየም ልታቀርባቸው የነበሩት ሦስት የሙዚቃ ዝግጅቶች ተሰርዘዋል።
በእነዚህ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ከ195,000 በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቅ ነበር።
ባለፈው ዓመት፣ ሞሃመድ ኤ በመባል የሚታወቀው የ16 ዓመት ሶሪያዊ ታዳጊ በጥቃቱ ምክንያት በጀርመን ፍርድ ቤት የ18 ወራት የእስር ቅጣት ተፈርዶበታል። በወጣቶች የወንጀል ሕግ መሠረት ሳይታሰር ቀርቷል።
በአጠቃላይ፣ ቤራን ኤን ጨምሮ ሦስት ሰዎች እአአ በ2024 በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በወቅቱ ሁሉም በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ።
በወንጀል ድርጊቱ ዋና ተጠርጣሪ በሆነው በቤራን ኤ ላይ የቀረቡት ክሶች ሰኞ ዕለት በቪየና አቃቤ ሕግ ቢሮ ይፋ ሆነዋል።
በክሱ መሠረት በኦንላየን መመሪያ ተቀብሎ ትሪአሴቶን ትሪፐርኦክሳይድ (ቲኤቲፒ)ን በመጠቀም ተቀጣጣይ ቦምብ ሠርቷል።
ታዳጊው የሠራው የቦምብ ዓይነት "አይኤስ ለጥቃቶች የሚጠቀምበት" ዓይነት ነበር ሲል በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
እንዲሁም የቦምብ ጥቃት እንዴት እንደሚፈጽም ከአይኤስ አባላት ምክር ጠይቆ እንደነበር ይታመናል።
ቤራን ኤ በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት አልሰጠም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እአአ በ2024 ታዳጊዎቹ በርካታ የኮንሰርት ተመልካቾችን ለመግደል አቅደው እንደነበር ተናግሯል።
መርማሪዎቹ ቤራን ኤ እንደ አውሮፓውያኑ በመጋቢት 2024 በዱባይ ጥቃት ለመፈጸም አቅዶ እንደነበር ጠቁመዋል።
በወቅቱ የነበሩ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በአንድ ጊዜ ሦስት የአይኤስ ጥቃቶችን ለመፈጸም የተቀናጀ ሴራ የተደረገ ቢሆንም፣ ነገር ግን ቤራን ኤ በመጨረሻው ደቂቃ ሀሳቡን ቀይሯል።
ቴይለር ስዊፍት ከሁለት ዓመት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራችው ጽሑፍ የቪየና ዝግጅቷ መሰረዝን "አሳዛኝ" ስትል ገልጻዋለች።
"ግን ደግሞ ባለሥልጣናቱን በጣም አመሰግናለሁ፤ ምክንያቱም ምስጋና ለእነሱ ይሁን፤ ይሄኔ በሐዘን ማቅ ለብሰን ነበር" ስትል አክላለች።















