የዓለም ገበያ ሲቃወስ የወርቅ ዋጋ ከ4 ሺህ ዶላር በላይ አሻቀበ

ጥፍጥፍ ወርቅ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

ባለሃብቶች በዓለም ላይ ባሉ የፖለቲካ እና የምጣኔ ኃብት አለመረጋጋቶች ገንዘባቸውን የት ማስቀመጥ እንዳለባቸው በተቸገሩበት በአሁኑ ወቅት ወርቅ ከፍተኛ የተባለውን የሽያጭ ዋጋ አስመዘገበ።

ወርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ከ4 ሺህ ዶላር በላይ ሆኗል።

ወርቅ እአአ ከ1970 ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋው የጨመረ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ ዓለም አገራት ላይ ታሪፎችን መጣላቸውን ካሳወቁ ወዲህ ከ25 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

ተንታኞች ባለሃብቶችን የበለጠ የሚያስጨንቀው የአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ ጠቃሚ የኢኮኖሚ መረጃዎች ይፋ አለመሆናቸው መሆኑን ይናገራሉ።

ወርቅ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን የገበያ ዋጋ መዋዠቅ ወይንም የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ሲያጋጥም ዋጋውን ጠብቆ እንደሚቆይ ወይንም እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ረቡዕ ዕለት ከሰዓት በእስያ የወርቅ ዋጋ ከ4021 ዶላር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል።

የገበያን መንፈስ ለመለካት የሚያገለግለው ጎልድ ፊውቸርስ እአአ ጥቅምት 7 የነበረበት ጣሪያ ላይ ደርሷል።

ጎልድ ፊውቸርስ ቀን በተቆረጠለት ጊዜ ለመገበያየት የሚደረግ ስምምነት ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ቢሮዎች መዘጋት "የወርቅ ዋጋን የሚያካልብ" ነው ሲሉ በሲንጋፖር መቀመጫቸውን ያደረጉት የኢሲቢሲው ባንከኛ ክርስቶፈር ዎንግ ተናግረዋል።

የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ባለሃብቶች አሁንም አስተማማኝ ኢንቨስትመንት ነው ወደሚሉት ወርቅ ፊታቸውን አዙረዋል።

በትራምፕ የመጀመርያው የሥልጣን ዘመን ለአንድ ወር ያህል የፌደራል ቢሮዎች መዘጋታቸውን ተከትሎ የወርቅ ዋጋ በ4 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።

የተወሰኑ ባለሃብቶች የፌደራል ቢሮዎች ረዥም ጊዜ ተዘግተው የማይቆዩ ከሆነ የወርቅ ዋጋ መልሶ መውረዱ አይቀርም ብለው እንደሚገምቱ ዎንግ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር የወርቅ "ያልተገመተ የዋጋ ጭማሪ" የተንታኞችን ግምት ያፈረሰ መሆኑን የዩኦቢ ባንክ ኃላፊ ሄንግ ኩን ሆው ተናግረዋል።

የወርቅ የዋጋ ጭማሪ ከአሜሪካ ዶላር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር የተገናኘ መሆኑንም የሚናገሩት ኃላፊው በርካታ መደበኛ ያልሆኑ ገዢዎች፣ የችርቻሮ ኢንቨስተሮች ወርቅም መግዛት ጀምረዋል ይላሉ።

ወርቅን የሚገዛ ሁሉ ጥፍጥፍ ወርቁን ይገዛል ማለት አይደለም።

የተወሰኑ ባለሃብቶች በወርቅ ዋጋ ተተምኖ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ ገንዘባቸወን ፈሰስ ያደርጋሉ።

በዚህ ዓይነት መልኩ እስካሁን ድረስ 64 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ የተደረገ መሆኑን ዓለም አቀፉ የወርቅ ምክር ቤት ንግድ ማኅበር አስታውቋል።