ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀይ መስቀል በጋዛ ስምንት የህክምና ባለሙያዎቹ መገደላቸው እንዳስደነገጠው ገለጸ
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማህበር በደቡባዊ ጋዛ፣ ራፋህ ሰብዓዊ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ስምንት የፍልስጤም የቀይ ጨረቃ ማህበር የህክምና ባለሙያዎች መገደላቸው እንዳስደነገጠው ገለጸ።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር ሰራተኞቹ የተገደሉት የእስራኤል መከላከያ ኃይል በፈጸመው ጥቃት ነው ብሏል።
ዘጠኝ ሰዎችን ጭኖ የነበረው አምቡላንስ አልሃሺን በተባለ ስፍራ ከሳምንት በፊት ከፍተኛ ተኩስ እንደተፈጸመበት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ገልጿል።
ለሳምንት ያህል ወደ ስፍራው መድረስ በመከልከሉ አስከሬናቸው ከሳምንት በኋላ እሁድ፣ መጋቢት 21/ 2017 ዓ.ም መወሰዱ ተገልጿል። አንድ የህክምና ባለሙያ አሁንም እንደጠፋ ነው።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር ከሰራተኞቹ በተጨማሪ ስድስት የሲቪል መከላለከያ ኤጀንሲ እንዲሁም አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኛ አስከሬኖችም ተገኝቷል ብለዋል።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር እንዲሁም ሐማስ ለህክምና ባለሙያዎቹ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።
ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ስምንቱ የፍልስጤም የቀይ ጨረቃ ማህበር የህክምና ባለሙያዎች አስከሬን "ለመጨረሻ ጊዜ ወደታዩበት ራፋህ አካባቢ እንዳንደርስ ከተከለከልን በኋላ፤ በሳምንቱ አስከሬናቸውን አግኝተናል" ሲል እሁድ ዕለት በመግለጫው አትቷል።
ተቋሙ የሞቱትን ስም የዘረዘረ ሲሆን እነዚህም ሙስጠፋ ክፉጋ፣ ሳሌህ ሙአመር፣ ኢዘዱን ሻዝ ፣ መሐመድ ባህሉል፣ መሐመድ አል ሃይላ፣ አሽራፍ አቡ ላብዳ፣ ራኢድ አል ሻሪፍ እና ሪፋት ራድዋን መሆናቸው ተገልጿል።
ሌላኛው የህክምና ባለሙያ አሳድ አል ናስራ ደብዛው ጠፍቷል ብሏል።
"ልቤ ተሰብሯል። እነዚህ ቆራጥ የአምቡላንስ ሰራተኞች የቆሰሉ ሰዎችን እያከሙ ነበር። ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ነበሩ" ሲሉ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበር ዋና ጸሐፊ ጃጋን ቻፓጌይን ተናግረዋል።
"መለያቸው የሆነውን አርማዎችን ለብሰው ነበር። አምቡላንሶቻቸው በግልጽ ምልክት ያለባቸው ናቸው" ብለዋል።
አክለውም "በጣም ውስብስብ በሆኑ የጦርነት ቀጣናዎች እንኳን ህጎች አሉ። ሰላማዊ ዜጎች እንዲሁም የሰብዓዊ ረድዔት ሰራተኞች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤ እነዚህም በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ ህግ በግልጽ የተቀመጡ ናቸው። የጤና አገልግሎቶችም ሊጠበቁ ይገባል" ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ስለ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ መግለጫ ምላሽ አልሰጠም።
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ አምቡላንሶች ላይ ባለፈው ሳምንት እሁድ መተኮሱን እንዳመነ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
አምቡላንሶቹ ላይ የተኮሰውም "አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች" ሆነው ስለታዩ መሆኑንም ገልጿል።
የእስራኤል ወታደሮች "በሐማስ ተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካታ የሐማስ አሸባሪዎችን ማስወገዳቸውን" መከላከያው ለኤኤፍፒ በላከው መግለጫ ገልጿል።
"ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ወታደሮቹ አጠራጣሪ ሁኔታ እየተጠጉ ነበር። ወታደሮቹ ወደ አጠራጠጣሪዎቹ ተሽከርካሪዎች በመተኮስ በርካታ የሐማስ እና የኢስላሚክ ጂሃድ አሸባሪዎችን ገድለዋል" ብሏል።
ሆኖም "ከመጀመሪያ ምርመራ በኋላ እነዚህ አንዳንድ አጠራጣሪ ተሽከርካሪዎች አምቡላንስ እና የእሳት አደጋ መኪናዎች እንደሆኑ ተደርሶበታል" ብሏል።
የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣና ባሴም ናይም ጥቃቱን አውግዘዋል።
"በአለም አቀፉ የሰብዓዊ ህግ መሰረት ጥበቃ ያላቸውን የነፍስ አድን ሰራተኞን ኢላማ አድርጎ መግደል የጄኔቫን ስምምነቶች በግልጽ የጣሰ እንዲሁም የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል።
እስራኤል የመጀመሪያው የጋዛ ተኩስ አቁም ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ ጥቃቷን ቀጥላለች። በባለፉት ሁለት ሳምንት በማይሞሉ ቀናትም 900 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል ከተኩስ አቁሙ በፊት በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።