በሱዳናውያን ላይ ከተፈፀመ የበቀል ጥቃት በኋላ ደቡብ ሱዳን የሰዓት እላፊ አወጀች

በሱዳናውያን ላይ የበቀል ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን የሰዓት እላፊ አወጀች።

ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀው ዜጎች ፍትህን በገዛ እጃቸው ከማስመለስ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ፕሬዚደንቱ ማሳሰቢያውን የሰጡት ከጎረቤት አገር ሱዳን መጥተው በአገሪቱ በሚኖሩ ሰዎች የንግድ ድርጅቶች እና ቤቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ነው።

በመዲናዋ ጁባ እና በሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ከተማ - አዌል ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭትም ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገልጿል።

ሆኖም የሟቾቹ እና ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ዜግነት አልተገለጸም።

በአዌል ከተማ ንብረትነታቸው የሱዳን ዜጎች የሆኑ ሦስት ቤቶች መቃጠላቸውንም የፖሊስ መኮንኖች ገልጸዋል።

የበቀል ጥቃቱ የተነሳው በቅርቡ የሱዳን ወታደሮች ደቡብ ሱዳናውያን ላይ ግድያ ሲፈፅሙ የሚያሳይ ቪዲዮ ከወጣ በኋላ ነው።

በአገሪቷ የተፈጠረውን ውጥረት ለማስቆምም ነው አርብ ዕለት የሰዓት እላፊ የተጣለው።

ኢንስፔክተር ጀነራል አብርሃም ማንዩዋት እንዳሉት ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ በጎዳናዎች ላይ ማንም መንቀሳቀስ እንዳይችል የተላለፈው እገዳ የተጣለው 'የሕዝብ እና የግል ንብረቶችን ከጥቃት ለመከላከል' ነው።

ሌላ የፖሊስ ምንጭም የፖሊስ መኮንኖች በጁባ የነበሩና አሁን በፖሊስ ጣቢያ ጥበቃ እየተደረገላቸው የሚገኙ 45 የሚሆኑ ሱዳናውያን ነጋዴዎችን ከጥቃቱ መታደጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአገሪቷ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ዋኡ ነዋሪ የሆኑና ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው የዓይን ምስክሮችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሱዳናውያን ነጋዴዎች በሚሰሩበት ታዋቂ በሆነው የገበያ ማዕከል-ሶክ ጃው ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሱቆችን ለመዝረፍ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ወጣቶቹን ለመበተን ፖሊስ ወደ ላይ ተኩሷል ብለዋል።

የሳልቫኪር የትውልድ ቦታ በሆነችው ቶንጂም አርብ ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱ ተነግሯል።

ቢቢሲ ከጁባ ውጭ ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት እና ዝርፊያ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ደቡብ ሱዳን ለረጅም ጊዜ ከቆየ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ነጻ አገር ለመመስረት ከሱዳን የተገነጠለችው እአአ በ2011 ነበር።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሱዳናውያን በአገራቸው ያለውን ጦርነት በመሸሽ ወደ ደቡብ ሱዳን እየተሰደዱ ነው።

ሱዳን እአአ ሚያዝያ 2023 ተዋጊ ጀኔራሎቿ እርስ በእርስ ግጭት ከጀመሩ አንስቶ በዓለም የከፋው ሰብዓዊ ቀውስ ያለባት አገር ሆናለች።

ግማሽ የሚያህለው [ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ] ሕዝቧ ምግብ እና እርዳታ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

በቅርቡም በዋድ ማዳኒ ከተማ የሱዳን ወታደሮች ሰላማዊ ደቡብ ሱዳናውያንን ሲገድሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቶ ነበር።

ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ግድያውን 'ጭካኔ የተሞላበት' እና 'ተቀባይነት የሌለው' ሲሉ የገለጹት ሲሆን የሱዳን መንግሥት መውጫ ያጡ በአገሪቷ የሚገኙ ደቡብ ሱዳናውያንን እንዲጠብቅና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ግድያውን እንዲመረምር አሳስበዋል።

የሰብዓዊ መብት ቡድኖችም ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 13 ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

የሱዳን ጦር በበኩሉ ግድያውን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠቱን ገልጿል።

ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች፣ ዘረኝነት በሱዳን ወረርሽኝ እንደሆነ ይናገራሉ። በእነዚህ ማሕበረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በገዚራ እና በዳርፉር በመሳሰሉ ቦታዎች ላይ ቀላ ያለ ቀለም ባላቸው የአርብ ተዋጊዎች እንደሚፈፀም ነው የሚነገረው።

እአአ በ2005 የእርስ በእርስ ጦርነቱ እስከሚያበቃ ድረስም 'ይኸው ድርጊት ቀጥሎ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ጥቁር አፍሪካዊቷ ደቡብ ሱዳን አረብኛ ተናጋሪ ከሆነችው ሱዳን እንድትገነጠል አድርጓታል።