ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናን ወታደራዊ ልምምድ 'ኃላፊነት የጎደለው' ስትል አሜሪካ ወቀሰች
ቻይና ድንበር ጥሳ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች በማለት ታይዋን መክሰሷን ተከትሎ አሜሪካ የቤጂንግን ድርጊት “ቀስቃሽ” እና “ኃላፊነት የጎደለው” ብላዋለች።
አራት ቀን ለሞላው ለቻይና ወታደራዊ ልምምድ ምላሽ ለመስጠት ታይዋን እሐድ ዕለት አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን ማሰማራቷ ተናግራለች።
ውጥረቱ የበረታው በዲሞክራት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ናንሲ ፔሎሲ የሚመራ የአሜሪካ ልዑክ ወደ ታይዋን ያደረገውን ጉዞ ተከትሎ ነው።
ጉብኝቱን በታይዋን ላይ ያላትን የሉዓላዊነት ጥያቄ ፈታኝ እንደሚያደርገው ቻይና ትገልጻለች። ታይዋን ደግሞ ራሷን የቻለች ሃገር እንደሆነች ትቆጥራለች።
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የቻይና መርከቦች እና አውሮፕላኖች በታይዋን ባህር ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ልምምዶች ሲያካሂዱ ነበር። አንዳንዶቹም ሁለቱን ወገኖች የሚለየው ኦፊሴላዊ ያልሆነ ድንበር ጥሰዋል።
የታይዋን ጦር በደሴቲቱ ላይ የተፈፀመ ጥቃት እንደሆነ ለገለፀው ድርጊት እሑድ ጠዋት በርካታ አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን በማሰማራት “ተገቢ” ምላሽ መስጠቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ-ቻንግ በታይፔ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቻይናን “በማን አለብኝነት” ልምምዶቹን በመቀጠል የአካባቢውን መረጋጋት ለማደፍረስ ተጠቅማለች ካሉ በኋላ ቻይና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ተማጽነዋል።
ቤጂንግ ስለሰሞኑ ልምምዶች ምንም አስተያየት አልሰጠችም። በታይዋን አካባቢ በአየር እና በባሕር አራት ቀናት የፈጀው ወታደራዊ ልምምድ እሑድ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዋሽንግተን ቻይና ውጥረቱን እያባባሰች ነው ስትል ወቅሳለች።
የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ "እነዚህ እንቅስቃሴዎች ቻይና ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ለውጥ ናቸው። ቀስቃሽ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው እና የተሳሳተ ስሌት ያከላተቱ ናቸው" ብለዋል።
"በታይዋን ባህር ዳርቻ ላይ ሠላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ከቆየው የረጅም ጊዜ ግባችን ጋር ይቃረናሉ።"
የፔሎሲ ጉብኝት በታይዋን የባህር ዳርቻ ሠላምና መረጋጋትን በእጅጉ አስጊ አድርጎታል ስትል ቻይና ገልጻለች።
ቻይና ታይዋንን ይዋል ይደር እንጂ በቁጥጥሯ ስር እንደምታውላት እንደ ተገነጠለች ግዛቷ ነው የምታያት። ታይዋን በበኩሏ ራሷን ከቻይና የተለየች አድርጋ የምትመለከት በራሷ የምትመራ ደሴት ነች።
በዓለም መሪዎች ለዚህ እውቅና መስጠት ቻይናን ያስቆጣል። በጉብኝቱ ምክንያት በፔሎሲ እና በቤተሰቧ ላይ ማዕቀብ መጣሏን ቤጂንግ አርብ ዕለት አስታውቃለች።